ቀጥታ፡

የመራጮች ምዝገባ ቀን መራዘሙ በምርጫው እንድንሳተፍ ተጨማሪ እድል ፈጥሮልናል

ደብረ ብርሃን  ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡-  የመራጮች ምዝገባ ቀን መራዘሙ በምርጫው እንድንሳተፍ ተጨማሪ እድል ፈጥሮልናል ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በደብረ ብርሃን ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች የምርጫ ካርድ ሳይወስዱ የቆዩ ነዋሪዎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤  ቦርዱ ለመራጮች ምዝገባ ቀን ያስቀመጠውን የጊዜ ሰሌዳ ማራዘሙ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ  ሁኔታዎችን ያመቻቸ ነው ብለዋል።

የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ በመመዝገብ ላይ የነበሩት የ65 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ  የሆኑት ወይዘሮ ጥሩነሽ ገብረወልድ ተጨማሪ የመራጮች ምዝገባ ቀናት እንዲኖር መደረጉ በምርጫው ተሳትፎ ለማድረግ እንድንችል አድርጓል ብለዋል ።


 

በምርጫው  ይጠቅመኛል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን የሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ በእውቀት ላይ ተመስርተን ለምርጫው እንድንዘጋጅ አድርጎናል ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አንዋር ደረጀ  እና ወይዘሮ ሰላም ሹመት ፤በተለያዩ ምክንያቶች የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ ሳይችሉ የቆዩ ቢሆንም በዛሬው እለት በተሰጣቸው የመጨረሻ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡


 

የመራጮች ምዝገባ ቀን መራዘሙ በምርጫው በመሳተፍ ለሀገር ሰላም ልማትና እድገት የሚጠቅም ፓርቲ ወደ ስልጣን ለማምጣት  እንድንዘጋጅ አድርጎናል ነው የሚሉት።

ወይዘሮ ጽጌ ታየ በበኩላቸው በመጨረሻው የምዝገባ ቀን የወሰዱትን የምርጫ ካርድ በጥንቃቄ በማስቀመጥ መብቴንና ጥቅሜን ያስጠብቅልኛል የሚሉትን ፓርቲ ወደ ስልጣን ለማምጣት እንደሚጠቀሙበትም ነው ያነሱት። 

ካርድ ያላወጡ ዜጎች በዛሬው እለት በሚካሔደው የመጨረሻው የመራጮች ምዝገባ ቀን ተጠቅመው የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸውም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም