መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚታዩ ችግሮች ወሳኝ መፍትሔ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚታዩ ችግሮች ወሳኝ መፍትሔ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፦ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚታዩ መሠረታዊ ችግሮች መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ወሳኝ መፍትሔ የሚሰጥ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎትን አስጀምረዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት፤ ከዓመታት በፊት የመንግሥት አገልግሎቶች ዜጎችን ለብልሹ አሰራርና እንግልት በመዳረግ የዘመናት ጥያቄ ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ይህም የዜጎችን ምሬት በማባባስ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጎትት እንደነበር አስገንዝበዋል።
በዚህም ለአገልግሎት የጥራት ችግር መፍትሔ ለማበጀት በመንግስት ደረጃ ተከታታይ ምክክር በማድረግ የዲጂታላይዜሽን ምኅዳር መፍጠር እንደተቻለ አንስተዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የመንግሥትን አገልግሎት ከደላላና ከሰው ንክኪ ነፃ የአሰራር ሥርዓት ለዜጎች በማቅረብ አገልግሎትን የሚያሳልጥ ምኅዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።
ይህም የሥራ ቅልጥፍን በማሳለጥ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ትላልቅ የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዜጎች በማቅረብ የተገልጋዮችን ፍላጎት የሚያሳልጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አንስተዋል።
ዜጎች የመንግሥትን አገልግሎት በነፃነት የማግኘት መብት አላቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህም ዜጎች መንግሥት የዘረጋቸውን ዘመናዊ የአሰራር ስርዓቶች በመጠቀም ግብርን በግልፀኝነት መክፈል እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
በአጠቃላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ይስተዋል የነበረውን መሠረታዊ ችግር መፍትሄ የሚሰጥ ወሳኝ አሰራር መሆኑን አስረድተዋል።
ዜጎችም የመንግሥትን ዘመናዊ፣ ግልፅና ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት ሊጠቀምበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።