የመመዝገቢያ ቀን መራዘሙን ተጠቅመን የምርጫ ካርድ ወስደናል- የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመመዝገቢያ ቀን መራዘሙን ተጠቅመን የምርጫ ካርድ ወስደናል- የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች
ወላይታ ሶዶ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- የመመዝገቢያ ቀን መራዘሙን ተጠቅመው የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ያራዘመው የመራጮች ምዝገባ ቀነ ገደብ ዛሬ ይጠናቀቃል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች የመራጮች ምዝገባ ቀን መራዘሙ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም የሚበጃቸውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን እድል የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል ።
በዚህም ዘግይተውም ቢሆን በዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፈው መምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ አብነት ኤልያስ፤ በስራ ምክንያት ካርድ ሳይወስዱ መቆየታቸውን ጠቁመው ጊዜው ሳይጠናቀቅ የመምረጥ መብታቸውን ለመጠቀም ካርድ መውሰድ በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምርጫ ቦርድ ባመቻቸው ተጨማሪ ቀን በወሰዱት የመራጭነት ካርድ የመምረጥ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።
የምርጫ ካርድ በመውሰድ መብቴን ለመጠቀም ስጠባበቅ ቆይችያለሁ ያለችው ደግሞ ወጣት ቤዛ አዲላ ናት።
የመምረጥ ዲሞክራሲያዊ መብት የሚወሰነው በምርጫ ካርድ ብቻ በመሆኑ ጊዜው ሳይጠናቀቅ ካርድ በመውሰዴ ዕድለኛ ነኝ ብላለች።
የምርጫ ሂደቱ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዜግነት ግዴታዋን እንደምትወጣም አስረድታለች።
ወጣት ታምራት ደስታ በበኩሉ ተጨማሪ ቀኑን በመጠቀም ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ መውሰዱን ገልጿል።
በካርዱ ለሀገር ልማትና ዕድገት ይበጃል ያለውን ፓርቲ የመምረጥ መብቱን እንደሚጠቀምም ነው የገለጸው፡፡
በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።