ቀጥታ፡

በተለያዩ ምክንያቶች የምርጫ ካርድ ሳይወስዱ የቆዩ ነዋሪዎች በመራጮች ምዝገባ ማጠናቀቂያ ቀን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ነው

‎ባሕርዳር፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡-  በባህርዳር ከተማ በስራ መደራረብና በተለያዩ ምክንያቶች የምርጫ ካርድ ሳይወስዱ የቆዩ ነዋሪዎች በመራጮች ምዝገባ ማጠናቀቂያ ቀን ተገኝተው ለመራጭነት የሚያበቃቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ነው።‎

‎‎በባህርዳር ከተማ የራስ አገዝ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ለሚ ጉርሙ በስራ መደራረብ ምክንያት ተመዝግበው የምርጫ ካርድ ሳይወስዱ መቆየታቸውን ገልፀዋል።


 

‎‎የመራጮች ምዝገባ ማጠናቀቂያ ቀን ዛሬ በመሆኑ የምፈልገውንና ለሀገሪቱ እድገት ይበጃል ብዬ ያመንኩበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችለኝን የምርጫ ካርድ ወስጃለሁ ብለዋል።

‎‎የሽምብጥ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ወጣት አለባቸው አባት በበኩሉ በግንዛቤ እጥረት ፈጥኖ የመራጭነት  ካርድ ሳይወስድ መቆየቱን ተናግሯል።


 

ይሁንና የመራጮች የምዝገባ ጊዜ ሰሌዳ ተራዝሞ መቆየቱ ዲሞክራሲያዊ መብቱን እንዲጠቀም እድል እንደፈጠረለት ጠቁሞ በመራጮች የምዝገባ ማጠናቀቂያ ቀን ተገኝቼ ለመራጭነት የሚያበቃኝን ካርድ ወስጃለሁ ብሏል።

በወሰድው የምርጫ ካርድ በመጠቀም ለወጣቶች የስራ እድል ያመቻቻል፤ ለሀገር እድገት ይሰራል ያለውንና የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ ይዞ የሚቀርበውን ፓርቲ እንደሚመርጥ አመላክቷል።

የሴቶችን ሁለንተናዊ መብት ያስከብራል ብለው ያመኑበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ዛሬ ተመዝግበው መውሰዳቸውን የገለፁት ደግሞ  የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ የሽበር ካሳ ናቸው።


 

‎‎የሀገር ዕድገትና ብልፅግና የሚረጋገጠው የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ተጠቅመን የምንፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ ስንችል ነው፤ ለዚህም ዝግጁ ነኝ  ብለዋል።

‎‎ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት እሱባለው አስፋው በበኩሉ ዛሬ የመራጮች ምዝገባ መጨረሻ  ቀን በመሆኑ ዲሞክራሲያዊ መብቴን ተጠቅሜ ለመራጭነት የሚያበቃኝን የምርጫ ካርድ ወስጃለሁ ብሏል። 


 

‎‎በወሰድኩት የምርጫ ካርድ የሀገርን አንድነት አስጠብቆ ያስቀጥላል ብዬ ያመንኩበትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ሲል አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም