አርሶ አደሮችና ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሮችና ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል
አምቦ/ጭሮ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን በምዕራብ ሸዋ ዞን የአምቦ ወረዳ አርሶ አደሮች እና የጭሮ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።
በአምቦ ወረዳ የጎሱ ቆራ ቀበሌ አርሶ አደሮች፤ በምርጫው ለሀገርና ለወገን ይጠቅማል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል አርሶ አደር ጋሻው ሹም፤ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም በአካባቢያቸው የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን የሚያስቀጥል ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደር ኡርገሳ ታደሰም በተመሳሳይ፤ የያዙትን የመራጭነት ካርድ በመጠቀም ለሕዝብ ጥቅም ይቆማል ብለው ላመኑበት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት የምርጫውን ዕለት በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል።
በግንቦት ወር በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይወክለኛል ላሉት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት ካርድ መውሰዳቸውን የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ደመሳ መገርሳ ናቸው።
የአምቦ ወረዳ የጎሱ ቆራ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ካቤ ገታታ፤ ከየካቲት 28 ቀን ጀምሮ ሲከናወን የቆየው የመራጮች ምዝገባ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት በስኬት እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል የጭሮ ከተማ ወጣቶች ፌዴሬሽን ሰብሳቢ መሐመድ ሀሰን፤ በከተማው ሲካሄድ የቆየው የመራጮች ምዝገባ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ከፍተኛ የወጣቶች ተሳትፎ የታየበት መሆኑን ገልጿል።
ፌዴሬሽኑ ለምርጫው ስኬታማነት በ26 የምርጫ ጣቢያዎች 62 ታዛቢዎችን መመደቡንም ጠቁሟል።
ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ መልኩ በምዝገባው ሂደት የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር የገለጸው ሰብሳቢው፤ ወጣቶች በንቃት በመሳተፍ ለተጠቃሚነታቸው የሚሠራን አካል እንዲመርጡ ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑንም ተናግሯል።
የከተማው ወጣት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አብደላ መሐመድ በበኩሉ፤ ማህበሩን በመወከል የምዝገባ ሂደቱን ሲታዘብ መቆየቱን ገልጾ፤ ሂደቱ ቀልጣፋ፣ የቁሳቁስ አቅርቦት የተሟላና የሕዝብ ተሳትፎ የጎላበት መሆኑን አመልክቷል።
የከተማው ወጣቶች ማህበር እንደ አንድ የሲቪክ ማህበር የምርጫ ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣም አረጋግጧል።
ወጣቶች በምዝገባ ሂደቱ የነበራቸውን ንቁ ተሳትፎ በድምፅ አሰጣጥ ዕለቱም በመድገም የመራጭነት መብታቸውን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል።