ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ለህዝቡ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ትልቅ የምስራች ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ለህዝቡ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ትልቅ የምስራች ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነውን የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል አገልግሎት አስጀምረዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የከተማ አስተዳደሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ቢሮክራሲን ለመቀነስ እና ተገልጋዮችን ከእንግልት ለመታደግ ያስቻሉ የመሶብ የተቀናጀ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በስፋት ወደ ስራ አስገብቷል።

ይህ አዲስ አሰራር ከቢሮ ወጥቶ አገልግሎትን ወደ ህዝብ ተደራሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ይህ ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎ አሰጣጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መመሪያ ከተሰጠ በኋላ የከተማ አስተዳደሩ በከተማው የመጀመሪያውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጳጉሜን 5 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም እስካሁን  በቦሌ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ፣ አዲስ ከተማ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ስድስት የአገልግሎት ማዕከላት ተከፍተው ለሕዝቡ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በእነዚህ ማዕከላት ውስጥ ከ150 በላይ የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እንዲሰጡ ተደርጎ የተደራጁ ሲሆን፤ ይህም የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።

እስካሁን 150 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን መቻላችውን ጠቅሰው፤ ይህም የተገልጋዩን እርካታ 98 በመቶ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

አስቸጋሪ የነበረውን ቢሮክራሲ ያቀለለው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህዝቡ ትልቅ እፎይታ የፈጠረ ሲሆን፤ በቀጣይም ተጨማሪ አገልግሎቶች በዚሁ ሥርዓት ውስጥ ተካተው እንደሚቀጥሉ ከንቲባዋ አረጋግጠዋል።

ከንቲባ አዳነች እንደገለፁት፤ እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስም አምስት አዳዲስ የመሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት መስጫዎች ተከፍተው በይፋ ወደ ሥራ ይገባሉ።

አዲሱ ተንቀሳቃሽ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግስት ህዝብ ድረስ በመቅረብ አገልግሎት እንዲሰጥ በማስቻል አዲስ የአገልግሎት አድማስ የከፈተ ትልቅ የምስራች ነው ብለዋል።

ይህ ተነሳሽነት አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ተደራሽ እና ዘመናዊ በማድረግ፣ ነዋሪዎች ያለምንም እንግልት ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎት የሚሰጡ አውቶቢሶች አስተማማኝ የኤሌክትሪክና የኢንተርኔት መሰረተ ልማት የተሟላላቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

በአሁኑ ወቅት ስምንት የተለያዩ ተቋማትን በማሰባሰብ 36 አገልግሎቶች በአንድ ላይ በማቀናጀት ለህዝቡ በቅርበት እየተሰጠበት ይገኛልም ነው ያሉት።

ይህ ዘመናዊ የዲጂታል አሰራር የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ግልጽና ቀልጣፋ ከማድረጉም በላይ፣ አድሎአዊ አሰራሮችን በማስቀረት ረገድ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ከንቲባዋ ገልጸዋል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም