ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ከተሳትፎ ባለፈ መፍትሄ አቅራቢ በመሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች

ባህርዳር፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ከተሳትፎ ባለፈ መፍትሄ አቅራቢ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

በባህር ዳር ከተማ ''የብሪክስ አሁናዊ አቅሞች እና የኢትዮጵያ የልማት ትብብር ትኩረቶች'' በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው  ጉባኤ መካሔድ ጀምሯል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሐመድራፊዕ አባራያ በመድረኩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች።

በዚህም ተሳትፎዋን በማሳደግ በጥናት ላይ የተመሰረቱ የተደራጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በማቅረብ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የሚጠቅሙ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ገልፀዋል።

የብሪክስ ሚና እየጎላ መምጣቱን ጠቅሰው በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አለም አቀፋዊ አቅሞችን በማስተባበር እየገጠሙ የሚገኙ ችግሮች በትብብር መፍትሄ ያገኛሉ ብለዋል።

በማዕቀፉም ኢትዮጵያ የመፍትሄ ሀሳብ አፍላቂ በመሆን ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ እየተሳተፈች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

መድረኩ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በፈጠራና በቴክኖሎጂ እድገት ውስጥ የራሷን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችላት የሁለትዮሽ ትብብር ጭምር የሚካሄድበት መሆኑንም አስረድተዋል።

የብሪክስ ማዕቀፋ በተለይም በግብርና እና ስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና መሰል ዘርፎች ልምድ  የሚሰጥበትና የሚገኝበት መድረክ መሆኑንም አንስተዋል።

በጉባኤው የኢትዮጵያ የ2025 የብሪክስ ተሳትፎ እና ቀጣይ አገራዊ ትኩረቶች፣ የኢትዮጵያ የአካዳሚክ ምርምርና አሰላሳይ ተቋማት ትኩረት ከሚደረግባቸው መስኮች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። 


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ፖሊሲ ዋና አማካሪ አምባሳደር ሚኒልክ አለሙ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት አንዷ መሆኗ ቁልፍና መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።

ብሪክስ የዓለምን ህዝብ 50 በመቶ፤ የዓለምን ኢኮኖሚ ደግሞ  40 በመቶ የሚሸፍን መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቷን ታረጋግጣለች ነው ያሉት።

ብሪክስ የማይበገርና ዘላቂነት ያለው የትብብር ማእቀፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያን በባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲ በማሳተፍ ተጠቃሚነቷን ብሎም ተሰሚነቷን ያሳድጋል ብለዋል።

ይኸው ጉባኤ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለሌሎች ጠቀሜታ የሚውል የመፍትሔ ሀሳብ ማፍለቂያ መድረክ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም