በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ቅንጅታዊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ቅንጅታዊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ጅማ ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ብቁ እና ተወዳዳሪ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የማጠናከር ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
የጅማ ዞን ትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር በጅማ ከተማ የተጀመረ ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ ከዞኑ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ530 በላይ ተማሪዎች ይሳተፋሉ። ውድድሩ ለሚቀጥሉት 10 ቀናት እንደሚቆይም ተገልጿል።
በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ የታደሙት የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ካሳሁን ገላና (ዶ/ር)፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚረጋገጠው በትምህርት እና በቴክኖሎጂ ነው ብለዋል።
ጠንካራ የትምህርት ተቋማትን መገንባት የሚቻለው በዕውቀትም ሆነ በአካል የጎለበቱ ተማሪዎችን ማፍራት ሲቻል መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ግብ ለማሳካትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ከማድረግ ጎን ለጎን ትምህርት ቤቶች ተተኪ ስፖርተኞች ማፍሪያ ስፍራ እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።
የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፣በዞኑ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን የማስፋፋት፣ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የስፖርት ትጥቆችን የማሟላት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የጅማ ዞን ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚፍታ አብዱልቃድር እና የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጉማ መኮንን፣ በዞኑ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ስፖርትን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከትምህርት ቤቶች የወጡ ወጣቶች በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ማስጠራት መቻላቸውን አስታውሰው፣ ነገ አገርን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት የትምህርት ተቋማትን የመደገፍና የማበረታታት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከሲጊሞ ወረዳ የመጣው ተማሪ መሀመድ ከሊፋ እና ከሰቃ ጨቆርሳ የመጣችው ተማሪ ተንዚላ ዛኪር በሰጡት አስተያየት፤ በትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ እንደ ፍላጎታቸውና ተሰጥኦዋቸው በሳምንት ሦስት ቀን ልምምድ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
አስፈላጊው ስፖርታዊ ትጥቅና የመለማመጃ ስፍራም እንደተመቻቸላቸው ተናግረዋል።