የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ለማረጋገጥ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ለማረጋገጥ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል
ጅማ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ምሁራን አስገነዘቡ።
በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ እና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር መንግሥቱ መላ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ሊሸከም የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የባሕር በር ባለቤትነት መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
ሀገሪቱ ቀደም ሲል የነበራትን የባሕር በር ያጣችው ያለ ሕጋዊ መንገድ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት በቂ የታሪክ እና የሕግ መሠረት እንዳለው አመላክተዋል።
የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናው የጋራ ልማትም ወሳኝ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።
መንግሥት የጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማሳካትም የሁሉም ዜጎች የተቀናጀ ድጋፍ እና ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የባሕር በር ጉዳይ ከኢኮኖሚ ባሻገር የሀገርን ደኅንነት የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ያስገነዘቡት ደግሞ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሊክስ እና የውኃ ሀብት ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል መምህር ዋቅጅራ ታከለ (ዶ/ር) ናቸው።
ባለቤትነትን ማረጋገጥ የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በማሳለጥ፣ የተጀመረውን ዕድገት በማፋጠን ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ቀጣናዊ ተወዳዳሪነትን ይፈጥራል ብለዋል።
መንግሥት የጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ መርኅ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ ሀገሪቱ ለቀይ ባኽር ያላት ቅርበትና ከመልማት መብቷ ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት ጉዳዩ የትውልዱ የማይቋረጥ ጥያቄ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል።