የክልል የሕዝብና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ የኢትዮጵያ የብዝሃነት ስዕል የሚንጸባረቅባቸው ተቋማት ናቸው-አቶ እውነቴ አለነ - ኢዜአ አማርኛ
የክልል የሕዝብና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ የኢትዮጵያ የብዝሃነት ስዕል የሚንጸባረቅባቸው ተቋማት ናቸው-አቶ እውነቴ አለነ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡-የክልል የሕዝብና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ የኢትዮጵያ የብዝሃነት ስዕል የሚንጸባረቅባቸው ተቋማት መሆናቸውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባለፉት ሶስት ወራት በክልል የህዝብ እና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያደረገውን የይዘት ስርጭት ክትትልና ግምገማ ውጤት ይፋ ማድረጊያ መርሀ ግብር አዘጋጅቷል።
"መገናኛ ብዙሃን ለሀገር ግንባታና ለማህበረሰብ አመለካከት ቀረፃ" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው መርሀ ግብር ላይ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራልና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና የተለያዩ የክልል የህዝብና የማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች ተገኝተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በመገናኛ ብዙሃን ላይ አበረታች ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ነው።
የክልልና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን የህዝብን ፍላጎትንና ችግሮችን በቅርበት በመለየት ተደራሽ ማድረግ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በክልሎች ማህበረሰቡን በሚያወያይበት ወቅት ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ በማድረግ የጎላ አበርክቶ እንደነበራቸውም ተናግረዋል።
እነዚህ የክልል የሕዝብና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ የኢትዮጵያን ብዝሃነት ስዕል የምናይባቸው ተቋማት ናቸው ብለዋል።
የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ያላቸውን አቅም አሟጠው በመጠቀም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መልካም ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ የክልል የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን አቅማቸውን የሚያጠናክሩበት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልል የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ወጥ ዘገባ መስራት መጀመራቸውን ገልጸው፤ በብሔራዊ መግባባት ላይ የጋራ አቋም መያዝ ጀምረዋል ብለዋል።
የክልል የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን አስተሳሳሪ ትርክት ለመገንባት በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተናብበው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በድህረ እውነት ዘመን የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ፈታኝ በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ቁልፍ ሥራ እውነትን ፈልጎ ማውጣት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።