ቀጥታ፡

አዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት የሚፈለገው አገልግሎት ወደ ህዝቡ እንዲጠጋ የማድረግ እድልን ይፈጥራል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ህዝብ ወደ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች መሄድ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ራሱ ወደ ህዝቡ እንዲጠጋ የማድረግ እድልን ይፈጥራል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች፥ ዛሬ በአይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነውን የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት መስጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማስጀመራቸውን ገልጸዋል።


 

የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ህዝብ ወደ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች መሄድ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ራሱ ወደ ህዝቡ እንዲጠጋ የማድረግ እድልን ይፈጥራል ብለዋል።

የተንቀሳቃሽ አውቶቢስ የአዲስ መሶብ አገልግሎትን በተሟላ ደረጃ አገልግሎት የጀመረ ሲሆን ህዝባችን በአለበት ቦታ ሆኖ አገልግሎት እንዲያገኝ እድል ይፈጥራል።

በአውቶቢሱ ላይ የአገልግሎት መስጫ ሥራ፣ የሀይል አማራጭ ሥራ (ከፀሓይ ብርሃን)፣ ፈጣን የኔትወርክ አማራጭን (MPLS = Multi Protocol Label Switching) በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ተደርጓል፣ የካሜራ ገጠማ እና የኮንፊግሬሽን ሥራ ተጠናቋል፣ የአገልግሎት መስጫ መሠረታዊ ግብዓቶች ተሟልቶ፣ የሙከራ አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ ተደርጓል።

ከቴክኖሎጂ ዝግጅት አንፃር ወጪን የሚቆጥብ (በየማዕከላቱ የዳታ ማዕከል ግንባታን የሚያስቀር)፣ የአገልግሎት ጥራት እና ወጥነትን የሚያረጋግጥ፣ በሁሉም ማዕከላት ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የUnified Infrastructure Model ተግባራዊ ማድረግ መቻላችን ስናበስር በታላቅ ደስታ ነዉ።


 

ተንቀሳቃሽ የአውቶቢስ አገልግሎት የተጀመሩ አገልግሎቶች፦

በመሶብ የአንድ ማዕከል፥

- የገቢ አገልግሎት (አዲስ ቲን ማውጣት)

- የንግድ አገልግሎት (ንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ ማደስ)

- የጤና (ለመንጃ ፈቃድ አካላዊ የጤና ምርመራ)

- የሲቪል ምዝገባ (የመታወቂያ ዕድሳት እና ልደት)

- የአሸከረካሪ ተሽከርካሪ (የመንጃ ፈቃድ እና የቦሎ ዕድሳት)

- የኢትዮ ፖስታ (የመንገድ ፈንድ ክፍያ)

- የብሔራዊ መታወቂያ (አዲስ ምዝገባና የመረጃ እርማት)

- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (ቅድመ ክፍያ)

የሚሰጡ አገልግሎቶች ናቸው።


 

በከተማችን ብሎም በሀገራችን ለዘመናት የአገልግሎት ዘርፉን ለመለወጥ ሳይቻል ስር በሰደደ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ተተብትቦ የኖረ ቢሆንም መንግስት ቃል በገባው መሰረት ችግሩን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ የሚለውጥ 'የመሶብ' ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በመተግበር ለተገልጋዩ ታላቅ ሽግግር እና እፎይታን ይዞ መጥቷል።

አክለውም፥ ለሕዝባችን የምናቀርበዉ ባዶ ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን የገባነውን ቃል ሁሌ በታማኝነት በተግባር ተከታታይነት ያለው የማያቋርጥ ተግባር እያከናወን ነዉ ብለዋል።

#ኢዜአ #Ethiopian_News_Agency

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም