ቀጥታ፡

የምዝገባ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት የመራጭነት ካርድ ወስደናል - የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች

አሶሳ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የመራጮች የምዝገባ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ዛሬ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ የተገለጸ ሲሆን፤ በተለያየ ምክንያት ሳይመዘገቡ የቀሩ ዜጎችም ካርድ እየወሰዱ ይገኛሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጭዎች እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ጊዜን በማራዘሙ በተለያየ ምክንያት ሳይመዘገቡ የቀሩ ዜጎች ዕድሉን እንዲያገኙ አድርጓል።



 
ወይዘሮ በላይነሽ ተርፋሳ በሰጡት አስተያየት፤ ዛሬ ያወጣሁት ካርድ በምርጫው ዕለት ለሀገር እና ለሕዝብ ይበጃል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ ይረዳኛል ብለዋል።

ወጣት ጉታ ቀጄላ እና ወጣት ራህመት ዩኑስ በበኩላቸው፤ የወጣቶችን የወደፊት ተስፋ የሚያለመልም ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መያዛቸውን ተናግረዋል።


 

በድምፅ መስጫ ዕለት ቁጭት እንዳያድርብን የመጨረሻው ቀን ላይ ካርዳችንን ወስደናል ያሉት ወጣቶቹ፤ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንደሚፈልግ ገልጸዋል። 



 
ዜጎች በቀረችው ጊዜ ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ እንደሚገባ ያስገነዘበው ደግሞ ወጣት ያደታ ቤኩማ ነው።
 
የመራጭነት ምዝገባ መራዘሙ ዜጎች በምርጫው ተሳታፊ እንዲሆኑ ዕድል መፍጠሩንም አንስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም