መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምና የወል ትርክትን መገንባት የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምና የወል ትርክትን መገንባት የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- መንግሥት ከለውጡ ወዲህ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን በማሻሻል ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብርና የወል ትርክት መገንባት የሚያስችል ዕድል መፍጠሩን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ።
ባለሥልጣኑ ባለፉት ሦስት ወራት በክልል የሕዝብ እና የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ላይ ያደረገውን የይዘት ሥርጭት ክትትልና ግምገማ ውጤት ይፋ ማድረጊያ መርሐ-ግብር አዘጋጅቷል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሐይማኖት ዘለቀ እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙኃን ለማኅበረሰብ አመለካከት ቀረፃና ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና አላቸው።
መገናኛ ብዙኃን ወቅታዊ መረጃ በመስጠት ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበርና የወል ትርክትን መገንባት እንደሚያስችሉም አስረድተዋል።
ከለውጡ ወዲህ የመረጃ ተደራሽነትን ለማሳደግ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መውጣቱንም አውስተዋል።
በዚህም መገናኛ ብዙኃን በዓይነት፣ በጥራት፣ በቋንቋ ብዝኀነት እና በሥርጭት አድማሳቸው እያደጉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ብቃት ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ለሀገር ብልጽግናና ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸው፤ የወል ትርክትን በመገንባት ለሀገር ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።