ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው

ሐዋሳ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት በአፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (AGRA) የቦርድ ሊቀመንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።


 

ሊቀመንበሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ከሀገር ባለፈ አህጉራዊ የልማት ትብብርና ትስስርን መሰረት ባደረገ መልኩ በስኬት መቀጠሉን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዋ ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች አስደናቂ መሆናቸውን አውስተው፤ እንደ ሀገር ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል።



 

ባለፉት ዓመታት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸው የተፈጥሮ ሃብትን ከመጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትና መሰረት መሆናቸው በተግባር ታይቷል ብለዋል።
 
በመሆኑም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት በአፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ነው ያመላከቱት።


 

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱም ለግብርና ልማትና ምርታማነት መሰረት እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።

የዘርፉ ልማት ቀጣይነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ችግኞችን መትከል እንዳለ ሆኖ፤ የተተከሉትን የመጠበቅና የመንከባከብ ልምድ እየዳበረ መሄድ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም