ቀጥታ፡

በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት ተደርጓል

ሐረር፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት መደረጉን የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ነገዎ ተናገሩ።


 

ኃላፊው ለኢዜአ እንዳሉት፤ በ2018 የትምህርት ዘመን ከ2 ሺህ 560 በላይ ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናውን በበይነ መረብ ይወስዳሉ።

የተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔ ካለፈው ዓመት በእጥፍ ለማሳደግ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።

ለዚህም፤ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ የቤተ-መጻሕፍት የአገልግሎት ጊዜን በማራዘምና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ተማሪዎችን የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑን ነው ያብራሩት።

ግብዓት ከማሟላት ባለፈ ተማሪዎች በጋራ እንዲያጠኑና እንዲያነብቡ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመው፤ በሞዴል ፈተናዎች እንዲለማመዱ መደረጉንም አክለዋል።

የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት ሀብታሙ ሱልጣን እና ሜላት ዓለማየሁ በሰጡት አስተያየት፤ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም