ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚላመድ የልማት ግስጋሴዋን ቀጥላለች 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚላመድና የማይበገር የልማት ግስጋሴዋን በተጨባጭ ውጤቶች እያስመሰከረች መቀጠሏን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ጽሕፈት ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ፤ ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚላመድና የማይበገር የልማት ግስጋሴዋን በተጨባጭ ውጤቶች እያስመሰከረች ቀጥላለች ብሏል። 

ይህ ጉዞ በተቀናጀ አሠራር ተመስርቶ፣ ከመቀነስ እስከ መቋቋም ድረስ የሚያካትት የልማት እርምጃዎችን በአስተማማኝ መንገድ አቀናጅቷልም ብሏል።

‎የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቀነስ የካርቦን ልቀትን መቆጣጠር፣ የደን ጭፍጨፋን በመከላከል እና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር 48 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል የሀገሪቱን አረንጓዴ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል ሲልም አብራርቷል።

በተመሳሳይ ጊዜ የውሃ አስተዳደርን ማዘመን እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተስማማ ግብርናን በመተግበር በምግብ ዋስትና ላይ የሚታይ ለውጥ አምጥቷል ነው ያለው።

‎በከተማ ልማት ዘርፍ የወንዝ ዳር ልማቶችን ማስፋፋት፣ አረንጓዴና ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን መገንባት እና ሞተር-አልባ ትራንስፖርትን ማስፋፋት ከተሞችን ከሥነ-ምህዳር ጋር የማስታረቅ አዲስ አቅጣጫ ፈጥሯል ተብሏል። 

በሀገር አቀፍ ደረጃም የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር ውሃን ለመስኖ ማዋል፣ ተስማሚ ዝርያዎችን መጠቀም እና የእንስሳት ሀብትን ማበረታታት፤ የሥርዓተ-ምግብ ዋስትናን እያጠናከረ ይገኛል ብሏል ጽሕፈት ቤቱ።

‎በኢነርጂ ዘርፍ የአረንጓዴ ኃይል ምንጮችን ማስፋፋት ልማትን የሚያነቃቃ ትልቅ ዐቅም ሆኖ ተገንብቷል ያለው ጽሕፈት ቤቱ፤ ለኢንዱስትሪና ለኤሌክትሪክ ትራንስፖርት መሠረት እየሆነም ነው ሲል ገልጿል።

እነዚህ ሁሉ ጥረቶች፤ ‎LT-LEDS: (የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ልማት ስትራቴጂ)፣ TYDP: (የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ)፣ NDC: (በሀገር አቀፍ ደረጃ የተተገበሩ ተሳትፎዎች)፣ NAP: (የሀገር አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ዕቅድ) ያሉ ማዕቀፎች እና የዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በተቀናጀ መልኩ በመተግበራቸው ኢትዮጵያ ለትውልድ የምታሻግረው ዘላቂ እና አረንጓዴ ነገን መሠረት እየጣለች ነው በማለት አብራርቷል።

ይህ ጉዞ ምላሽ ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያን ብሩህ መፃዒ ጊዜ የሚገነባ አቅጣጫ ነውም ብሏል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመረጃው።

#PMOEthiopia

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም