ማንችስተር ሲቲ የሊጉ መሪ ለመሆን ከበርንሌይ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ሲቲ የሊጉ መሪ ለመሆን ከበርንሌይ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ በርንሌይ ከማንችስተር ሲቲ በተርፍ ሙር ስታዲየም ይጫወታሉ።
በርንሌይ በ20 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ማንችስተር ሲቲ በ67 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ባለሜዳው በርንሌይ ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ያለውን ጭላንጭል ተስፋ ለማለምለም ያግዘዋል።
ማንችስተር ሲቲ ካሸነፈ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው የሊጉን መሪነት ከአርሰናል ይረከባል።
ማንችስተር ሲቲ በሳምንቱ መጨረሻ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር በሚያደርገው የኤፍኤ ካፕ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ምክንያት ፣ የ34ኛ ሳምንት ጨዋታውን ዛሬ አስቀድሞ ያደርጋል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ቦርንማውዝ ከሊድስ ዩናይትድ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በቫይታሊቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ቦርንማውዝ በ48 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት 13 የሊግ ጨዋታዎች አልተሸነፈም።
ቦርንማውዝ ካሸነፈ ባለመሸነፍ ጉዞው ይቀጥላል። በአውሮፓ መድረክ የመሳተፍ እድሉን ያሰፋል።
ሊድስ ዩናይትድ በ39 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን የሚያስመዘግብ ሲሆን ከወራጅ ቀጠና የሚርቅበትንም እድል ያገኛል።