ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ መንገድ

(በዮሐንስ ደርበው)

ታሪክ እንደሚነግረን፤ የአዕምሯዊ ንብረት ጥቅም ለመጀመሪያ ጊዜ ዕውቅና ያገኘው የኢንዱስትሪያዊ ንብረት ጥበቃን በሚመለከተው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1883 በተፈረመው የፓሪስ ስምምነት እንዲሁም፤ በ1886 የተፈረመውን የሥነ-ጽሑፍና ሥነ-ጥበብ ሥራዎች ጥበቃን የተመለከተውን የበርን(ስዊዘርላንድ) ስምምነት ተከትሎ ነው።

እነዚህ ስምምነቶችም በዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት የሚተዳደሩ መሆናቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣንን፤ በ2022 ዓ.ም ፈጠራንና ኢኖቬሽንን በማበረታታት የፈጠራ ሐሳቦችን ወደ ዕሴት በመለወጥ ሂደት ለሀገራዊ ብልጽግና ቁልፍ ሚና የሚጫወት በአፍሪካ ተምሳሌት የአዕምሯዊ ንብረት ተቋም ለማድረግ እየታተረች ነው።

ለዚህ ርዕይ መሳካትም፤ ተቋሙ የአዕምሯዊ ንብረት ሥርዓት ለሀገራዊ ፈጠራ መጎልበት፣ የኢኖቬሽን፣ ቴክኖሊጂ ሽግግር እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ማደግ ጥቅም ላይ የሚውልበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሀገራዊ የመዋቅር ሽግግርን መደገፍ የሚል ተልዕኮ አንግቦ እየሠራ ይገኛል።

የእስካሁኑ የንግድ ምልክት፣ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች እና የፈጠራ ባለቤትነት (ፓተንት) ምዝገባ


 

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ወርቅነህ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2015 ዓ.ም እስከ ያዝነው በጀት ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ድረስ በንግድ ምልክት፣ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች እና በፈጠራ ባለቤትነት (ፓተንት) 20 ሺህ 476 ምዝገባዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት ይላሉ፤ 14 ሺህ 729 የንግድ ምልክቶች፣ 5 ሺህ 254 የቅጅና ተዛማጅ መብቶች እንዲሁም 1 ሺህ 781 የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ምዝገባ በተቋማችን አማካኝነት ተከናውኗል።

የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ምንድን ናቸው?

አዕምሯዊ ንብረት ማለት በሰው ልጅ አዕምሮ የሚፈጠሩ የፈጠራ ሥራዎችን የሚመለከት መሆኑን የገለፁት አቶ ብሩክ፤ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች እንደማንኛውም ቁሳዊ ሀብት በንብረትነት የሚታወቁበትን አግባብ የያዘው ሥርዓት ደግሞ የአዕምሯዊ ንብረት መብት እንደሚሰኝ ያስረዳሉ።

በዚህ አግባብ፤ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች እንደማንኛውም ቁሳዊ ንብረት ሁሉ የፈጠራ ሥራዎችን ለሚያመነጩ ባለመብቶች የሚሰጡ የባለቤትነት መብቶች መሆናቸውን እንረዳለን።

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀርበው እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፤ ወጥ ሥራዎችን ለማመንጨት የፈጠራ ባለመብቶች ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን መስዋዕት በማድረግ ከብዙ ድካም በኋላ ያገኟቸው የፈጠራ ውጤቶች በመሆናቸው ነው።

ለአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ማድረግ ለምን አስፈለገ?

አንድም፤ የሰው ልጅ ቀጣይ ዕድገትና የኑሮ ደኅንነት ዋስትና መሠረት የሚያርፈው በቴክኖሎጂና ባሕል ዘርፎች በሚያሳርፋቸው ፈጠራዊ ብቃቶቹ በመሆኑ እንዲሁም የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን ለማካሄድ ተጨማሪ ሀብት የሚያስገኝ በመሆኑና ይህም የኢኖቬሽን ሥርዓቱን ስለሚያሳድግ ነው ይላሉ አቶ ብሩክ።

እንዲሁም፤ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃና ዘርፉን ለሕዝብ የማስተዋወቅ ተግባር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማረጋገጥ የድርሻውን ስለሚወጣና የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት በአጠቃላይ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በተሻለ ደረጃ ላይ እንዲቆም ስለሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም፤ ሀገራት ጠንካራ የአዕምሯዊ ንብረት ሥርዓት በፈጠሩ ቁጥር ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ የልማት መሣሪያ መሆኑን ይገነዘባሉ። ጠንካራና ፍትሐዊ የአዕምሯዊ ንብረት ሥርዓት በፈጠራ ባለቤቶችና በተጠቃሚው ሕዝብ ዘንድ ሚዛናዊ ነው ያሉት አቶ ብሩክ።

በአጠቃላይ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን በአጽነዖት አንስተዋል።

ዜጎች በአዕምሯዊ ንብረት ሥርዓት እንዴት ተጠቃሚ ይሆናሉ?

ባለብዙ ቢሊየን ዶላር የፊልምና ድምጽ ሪከርድስ አሳታሚዎችና ሶፍትዌር ኢንዱስትሪዎች ለብዙ ሚሊየኖች የመዝናኛ ሥራዎች የሚያበረክቱት የቅጅ መብት ጥበቃ በመኖሩ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም አቶ ብሩክ ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ተጠቃሚዎች የሚፈልጓቸውን ምርቶችና አገልግሎቶችን መለየት የሚያስችላቸው ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ምልክቶች ጥበቃና የመብት ማስከበር ሥርዓቶች ባይኖሩ ኖሮ ተመሳስለው በሚቀርቡ ምርቶችና አገልግሎቶች መታለልና ሌሎችም ችግሮች ያጋጥማቸው እንደነበርም ጠቁመዋል።

ስለዚህ ምርቶችን በመሸመት ሂደትም በምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ያለምንም ግራ መጋባት ግብይቱን ማከናወን እንደሚያስችላቸው መገንዘብ ይቻላል።

እንደ አቶ ብሩክ ገለጻ፤ ለፓተንት የፈጠራ ሥራዎች ጥበቃ በመደረጉ መሰጠት የሚገባቸው ማበረታቻዎች የማይሰጡ ከሆነ፤ የፈጠራ ባለሙያዎች ቀጣይ የምርምር ሥራዎችን ማሳደግና ማስፋት እንደማይችሉ ይገመታል። በቀጣይነት የሚገኙ የተሻሻሉ የፈጠራ ሥራዎች አለመኖራቸው ደግሞ፤ በምርቶች ተጠቃሚና አጠቃላይ የኑሮ መሻሻል ሂደት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

የአዕምሯዊ ንብረት ዓይነቶች እንዴት ይመደባሉ?

የአዕምሯዊ ንብረት፤ የኢንዱስትሪያዊ ንብረት (Industrial Property) እና የቅጅና ተዛማጅ መብቶች (Copyright and Related Rights) በሚሉ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች እንደሚመደብ ያስረዳሉ።

አክለውም፤ ኢንዱስትሪያዊ ንብረት በውስጡ፤ የፓተንት፣ የንግድ ምልክት፣ የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ እና የጂኦግራፊያዊ ምንጭ አመላካቾች የተሰኙ አራት ክፍሎችን እንደሚይዝ ያብራራሉ።

ፓተንት ምንድን ነው?፡- ፓተንት ማለት በአንድ ቴክኒካዊ ባሕርይ ባለው የፈጠራ ሥራ ላይ የሚኖር የፈጠራ ባለቤትነት ብቸኛ መብት መሆኑን አቶ ብሩክ አስረድተዋል። የፓተንት መብት በአንድ ምርት (ለምሳሌ ማሽን ወይም የአመራረት ሂደት (Process) ሊሰጥ የሚችል ሲሆን፤ ፈጠራውም ለአንድ ቴክኒካዊ ችግር መፍትሔ የሚያስገኝ መሆን ይኖርበታል ይላሉ። ከፈጠራ ሥራው አመንጪ ይሁንታ ውጭ ሥራውን ገበያ ላይ ማዋል፣ መጠቀም፣ ማሰራጨት፣ መሸጥ ወዘተ… እንደማይቻልም አክለዋል። ፓተንት ለባለ መብቱ የጥበቃ መብት የሚያስገኝ ሲሆን፤ የጥበቃው ዘመንም በአጠቃላይ እስከ 20 ዓመት ሊደርስ ይችላል።

ፓተንት የሚያስገኛቸው ሕጋዊ (የጥበቃ) መብቶች፡- የፈጠራ ሥራውን መጠቀም የሚችሉና የማይችሉ ሰዎችን መወሰን፤ ሦስተኛ ወገኖች ሥራውን እንዲጠቀሙ የመፍቀድ ወይም የፈቃድ ውል ስምምነት የመስጠት እንዲሁም የፈጠራ ሥራውን የመሸጥ (ለአዲስ የፓተንት ባለመብት) የሚሉት ይገኙበታል ብለዋል ሥራ አስፈጻሚው።

የፓተንት ሥራዎች ለምን ያስፈልጋሉ?፡- ይህን ሲያብራሩም፤ ፓተንት ለፈጠራ ባለመብቶች ዕውቅናንና ሽልማቶችን (ማበረታቻዎችን) የሚሰጥ በመሆኑ፣ ፈጠራዎቹ የኢኖቬሽን ሥራዎችን ስለሚያጠናክሩና በዚህም ቀጣይነት ያለው የሰው ልጅ ሕይወት መሻሻልን የሚያረጋግጥ በመሆኑ እና በሌሎችም በጎ አስተዋጽዖዎች ፓተንት በዕጅጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የንግድ ምልክት ምንድን ነው?፡- የንግድ ምልክት ማለት አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ከሌላው ምርትና አገልግሎት እንዲለይ ለማስቻል በንግድ ምልክት ባለቤቶች ለምርታቸውና አገልግሎታቸው መለያ እንዲሆን ጥቅም ላይ የሚውል ልዩ ምልክት መሆኑን ተናግረዋል። የንግድ ምልክት ሸማቹ ሕብረተሰብ የሚፈልገውን ምርትና አገልግሎት በቀላሉ ለይቶ እንዲገዛ ከማስቻሉም በላይ በሚገዛው ምርትና አገልግሎት ጥራት ላይ በመተማመን ፍላጎቱን እንዲያሟላ ያደርጋል።

የንግድ ምልክት ለባለመብቱ ምን ጥቅም ያስገኛል?፡- ምርቶቹ (አገልግሎቶቹ) በተጠቃሚዎች እንዲለዩለት ወይም እንዲታወቁለት ያደርጋል፣ ክፍያን መሠረት አድርጎ ሦስተኛ ወገን እንዲጠቀምበት የመፍቀድ፣ የንግድ ምልክቶች በራሳቸው ዋጋ አላቸው (የአዕምሯዊ ንብረት ዋጋ ትመና (IP Valuation) ለምሳሌ በፈረንጆቹ በ2026 የመጀመሪያ ወራት አፕል (Apple) 600 ቢሊየን ዶላር፣ ማይክሮሶፍት (Microsoft) 565 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር፣ ጉግል (Google) 433 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ግምት እንደነበራቸው ተብራርቷል።

በተጨማሪም፤ የንግድ ምልክት በሕግ በሚቀመጥ የጊዜ ገደብ መሠረት እየታደሠ ለዘላለም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፤ የንግድ ምልክት ባለቤቱን በማስተዋወቅ ዕውቅናና የገንዘብ ትርፍን ያስገኛል፤ የንግድ ምልክት ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ውድድሮችን በመግታት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል (ተመሳስለው የሚሠሩና ለገበያ የሚቀርቡ ሥራዎችን (Counterfieited Products) ለመዋጋት ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፤ የንግድ ምልክት ሰዎች ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን ሚዛናዊ በሆነ አግባብ እንዲያቀርቡ በማድረግና በብሔራዊና ዓለም አቀፍ ደረጃ የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አስተዋጽዖው የላቀ ነው ብለዋል።

ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ምንድን ነው?፡- ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ በምርቶች ሥነ-ውበት (Esthetics) ላይ ተመስርቶ ቅርጽን፣ መስመሮችን ወይም ቀለምን በመጠቀም ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የገዥዎችን (ሸማቾችን) ቀልብ ለመሳብ እንዲችሉ በምርቶች ላይ የሚገለጽ የንድፍ ጥበብ ዘርፍ ነው ያሉት አቶ ብሩክ፤ ኢንዱስትሪያዊ ንድፎች በኢንዱስትሪና ዕደ-ጥበብ ምርቶች ላይ ተዘጋጅተው ሊወጡና ለገበያ ሊቀርቡ ይችላሉ ይላሉ።

ዘርፉ ከቴክኒካልና ሕክምና መሣሪያዎች አንስቶ እንደ ሠዓት፣ ጌጣጌጦችና ሌሎች የቅንጦት ምርቶች ዕቃዎችን ሊያካትት ይችላልም ብለዋል። የቤት ዕቃዎችን፣ የኤሌክትሪክ መሣሪያዎችን፣ ተሽከርካሪዎችና የሕንጻ ንድፎችን እንዲሁም የጨርቃጨርቅ ንድፍ ውጤቶች በኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሥር የሚወድቁ ይሆናሉ ይላሉ።  ኢንዱስትሪያዊ ንድፎች ጥበቃ የሚደረግላቸው አዲስ ወይም ወጥ ከሆኑ ብቻ መሆኑን ገልጸው፤ በዲዛይኑ ውስጥ ከሚገለጸው ምርት ጋር ተያያዥ የሆኑ የቴክኒክ ጉዳዮች ጥበቃ እንደማይደረግላቸው አስታውቀዋል።

ለኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ጥበቃ ማድረግ ለምን ያስፈልጋል?፡- በምርቶች ውበት ላይ የሚገለጽ በመሆኑ የተጠቃሚውን ዐይን ይስባል፣ የምርቶችን ዋጋ ይጨምራል፣ ፈጠራንና ውድድርን ያበረታታል፣ ለባለመብቱ ብቸኛ መብትን ያጎናጽፋል፣ በኢንዱስትሪዎች፣ ባሕላዊ ጥበብና በዕደ ጥበብ ዘርፍ ፈጠራ በማሻሻል ኢኮኖሚ እንዲያድግ ያደርጋል፣ የጭ ንግድን (Export Trade) ያሳድጋል በማለት የኢንዱስትሪ ንድፍ ጥበቃ አስፈላጊነትን ያብራራሉ።

የጂኦግራፊያዊ ምንጭ አመላካች ምንድን ነው?፡- የጂኦግራፊያዊ ምንጭ አመላካቾች በምርቶች ላይ የሚቀርቡ ምልክቶች ሆነው እነዚህ ምልክቶች አንድ የተወሰነ አካባቢን በምርቱ ምንጭነት የሚያመላክቱና ጥራትንና ዝናን ከቦታው ጋር አስተሳስረው የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን አቶ ብሩክ ያስረዳሉ።

በአብዛኛው የጂኦግራፊያዊ ምንጭ አመላካቾች ልዩ ምርቱ የሚገኝበትን የቦታ ስም (Specific Local Geographyical Factors – Climate, Soil) ይይዛሉ። ለምሳሌ፡- Roquefort for Cheese -France፣ የማረቆ በርበሬ፣ የሸኖ ቅቤ፣ የዓድኣ ጤፍ … የመሳሰሉት ምርቶች ተጠቃሾች ናቸው።

የጂኦግራፊያዊ ምንጭ አመላካቾችን መጠበቅ ለምን ያስፈልጋል?፡- ተጠቃሚዎች ምርቶች የሚገኙበትን ሀገር ወይም አካባቢ በቀላሉ ለመለየት፣ ሕጋዊነት በሌላቸው ወገኖች የምርቱ መገኛ አካባቢ እና የምርቱ ዝና በተሳሳተ መልኩ ለሌላ ምርት መጠሪያ እንዳይውል ለመከላከል ይረዳል ይላሉ።

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ምንድን ናቸው?፡- የቅጅ መብት በሥነ-ጽሑፍ እና ሥነ-ጥበብ ዘርፍ ወጥ የፈጠራ ሥራዎችን ለሚያመነጩ ደራስያን፣ አርቲስቶች ወዘተ… የባለቤትነት መብት የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍ መሆኑንም ነው ሥራ አስፈጻሚው የሚያስረዱት።

በአንጻሩ ተዛማጅ የቅጅ መብት ማለት ይላሉ አቶ ብሩክ፤ በወጥ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ተመስርተው የሚሠሩ ተዛማጅ (Related) የፈጠራ ሥራዎችን ያካትታል። ለምሳሌ፡- ከዋኞቹ (ተዋንያን እና ዘፋኞች)፣ ድምጽ ሪከርዲንግስ፣ አሳታሚዎች (ኮምፓክት ዲስኮች)፣ የብሮድካስት ተቋማት፣ (ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን) የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ ሲሉ ዘርዝረዋል።

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ምን ዓይነት መብቶች ያስገኛሉ?፡- ባለመብቶች ሥራዎቻቸውን ለመጠቀም ወይም ሦስተኛ ወገኖች እንዲጠቀሙባቸው የመፍቀድ፣ ሥራዎች እንዲባዙ፣ ለሕዝብ እንዲዳረሱ፣ እንዲሠራጩ፣ እንዲተረጎሙ ወይም ወደሌላ ሥራ እንዲቀየሩ የመፍቀድ ወይም የመከልከል፣ የደራሲነት (የአመንጭነት) መብት ዕውቅና እንዲያገኙ፣ በብዕር ስም የመጠቀም መብት፣ ክብሩንና መልካም ስሙን የሚያጎድፍ የሥራ መዛባት እንዳይኖር የመጠበቅ ወይም የሥራው ወደሌላ መቀየር የሚያስከትለውን ጉዳት የመቃወም ወዘተ መብቶችን ያስገኛሉ ብለዋል።

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ምን ጥቅሞች ያስገኛል?፡- የሰውን ልጅ የፈጠራና ኢኖቬሽን ጥረቶችን ያሳድጋል፣ ለፈጠራ አመንጭዎች መበረታታትን ይፈጥራል፣ የሕጋዊ ተፈጻሚነትን በማረጋገጥ አመንጭዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች መዋዕለ-ነዋይ እንዲያፈሱ የፈጠራ ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራቸውን የሥርጭት ሽፋን ያሳድጋል ነው ያሉት አቶ ብሩክ።

የፓሪስ ስምምነት አባል

ኢትዮጵያ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም የፓሪስ ስምምነት አባል ሀገር ለመሆን ለዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት (WIPO) ያስገባችው ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስምምነቱን ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በማጽደቁ ከዚሁ ዕለት ጀምሮ ለስምምነቱ ተገዢ ሆናለች።

አቶ ብሩክ እንዳብራሩት፤ የፓሪስ ስምምነት በጥቅሉ የኢንዱስትሪያዊ ንብረቶችን ጥበቃ የሚመለከት ነው። የፓተንት፣ የንግድ ምልክት፣ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ፣ የግልጋሎት ሞዴል (በአንዳንድ ሀገራት ሕግ ኢትዮጵያን ጨምሮ “የአነስተኛ ፈጠራ የባለቤትነት መብት” በመባል የተደነገገ)፣ የአገልግሎት ምልክት፣ የንግድ ስም (የኢንዱስትሪ ወይም የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው ስያሜዎች)፣ ጂኦግራፊያዊ አመላካች እና ፍትሐዊ ያልሆነ ውድድርን መከላከል ያካተተ ነው።

የስምምነቱ መሠረታዊ ድንጋጌዎች በሦስት ዋና ዋና መርሆዎች እንደሚከፈሉ ጠቁመው፤ እነሱም፡- የፓሪስ ስምምነት አባል ሀገር መሆን በሌሎች አባል ሀገራት ውስጥ እንደ ዜጋ የመስተናገድ መብት፣ የቀዳሚነት መብት የማግኘት፣ በቀላሉ ዓለም አቀፍ ጥበቃ የማግኘት አሠራር እና መሰል ጉልህ ጥቅሞችን የማግኘት ዕድል ይሰጣል ሲሉ ይገልጻሉ።

በመሠረቱ የፓሪስ ስምምነት የአዕምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃን በማቀላጠፍ አዳዲስ ግኝቶችንና ፈጠራዎችን እንዲሁም የንግድ ሥራዎች ድንበር ሳይገድባቸው የፓተንትና የንግድ ምልክት መብቶች በቀላሉ እንዲጠበቁ በማድረግ ፈጠራን፣ ንግድን እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን እውን ያደርጋል ብለዋል።

የዘንድሮው የአዕምሯዊ ንብረት ቀን

የፊታችን ሚያዝያ 17 ቀን 2018 ዓ.ም “አዕምሯዊ ንብረትና ስፖርት፤ እንዘጋጅ፣ እንጀምር፣ እንፍጠር!” በሚል መሪ ሐሳብ ዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

በስፖርት ዓለም ውስጥ የሚከሰቱ ተወዳዳሪዎች የግልና የጋራ ፈጠራዎች፣ ንድፎች፣ ብራንዶችና የመልካም ዝና ታሪኮችን ለመጠበቅና ሀገራትን ጭምር ለማስተዋወቅ የአዕምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ ሥርዓት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል።

ምክንያቱም ስፖርት በባሕርይው በውድድር ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን፤ ከሀገራት ዝና፣ ከፋሽን ዲዛይን፣ ከመዝናኛ፣ ከሚዲያ ሥርጭት፣ ከጤናና ከዕለት ተዕለት መገልገያ ቁሶች ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም