በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ አድርገዋል
ወላይታ ሶዶ፤ሚያዚያ 13/2018(ኢዜአ)፦በወላይታ ሶዶ ከተማ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
በከተማ አስተዳደሩ "አረንጓዴ አሻራ ለተምሳሌት ሀገር ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል የዘንድሮ የበልግ ወቅት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በመርካቶ ክፍለ ከተማ ቦሳ ዝጋ ቀበሌ ተካሂዷል።
የከተማው ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት ባላፉት የለውጡ ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት አረጋግጠዋል።
በመርሀ ግብሩ የተተከሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ሚዛኑን ለመጠበቅ እያገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የችግኝ ተከላ ሥራውን ለማስቀጠል የቡና፣ የእንሰት የአቮካዶና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ሙሉ ዝግጅት በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ቡሹራ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል።
ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ለተከላ ከተዘጋጁ ችግኞች ውስጥ 150 ሺህ የሚሆኑት የተሻሻሉ የቡና ዝርያ ችግኞች መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ምርታማነታቸው በምርምር የተረጋገጡ የእንሰት፣ የአቮካዶ እና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።
የሚተከሉ ችግኞች ውጤታማ እንዲሆኑም የተጠናከረ የባለሙያዎች ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች አቶ ደበላ ዳና እና አቶ ኤልያስ ጁና በውሃ ገብ መሬቶችና እና በእርሻ ማሳቸው ላይ ባህር ዛፎችን እና ያረጁ ቡናዎችን በመተካት ልማቱን ማከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በችግኝ ተከላው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ፍራፍሬዎችን በመትከል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን አንስተዋል።
በዘንድሮ የአረንጎዴ አሻራ መርሃግብርም የቡና ችግኝ በስፋት ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ነው የገለጹት።
አርሶ አደሮችም በመርሀግብሩ ቡናና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞችን ተክለው በመንከባከብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ አሳስበዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የዞንና የከተማ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።