ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የዜጎችን የፈጠራ ክህሎትና የስታርት አፕ ተወዳዳሪነት እያጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የዜጎችን የፈጠራ ክህሎትና የስታርት አፕ ተወዳዳሪነት እያጎለበተ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ሀገር በቀል ዕውቀትን በማበረታታት የዜጎች የፈጠራ ክህሎትና የስታርት አፕ ተወዳዳሪነት እንዲጎለብት ማድረጉን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
በማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለቀጣዩ የዕድገት ምዕራፍ ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትልም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን በማስፋት የስታርት አፕ ፈጠራን የማበረታታት ተግባር ቁልፍ ተግባር እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በዛሬው ዕለትም ኮከብ የተሰኘ የዲጂታል ፕላትፎርም የሕጻናትን ዝንባሌ የሚመጥን ሳቢ የመማሪያ የዲጂታል ሥርዓት ይፋ አድርጓል።
በዚሁ ወቅት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የቴክኖሎጂ አማካሪ ሻምበል ይልማ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን ዕድገት ለማሳለጥ ፈጠራን ማበረታታት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አቅጣጫም ሀገር በቀል ዕውቀትን በማበረታታት የዜጎች የፈጠራ ክህሎትና ስታርት አፕ ተወዳዳሪነት እንዲጎለብት ማድረጉን ገልጸዋል።
የፈጠራ ክህሎት ማበረታቻ የሕግና የፖሊሲ አቅጣጫም ሀገር በቀል ዕውቀትን በማጎልበት የዲጂታል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኮከብ ዲጂታል ፕላትፎርም መምህራንና ተማሪዎችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ የፖሊሲ አቅጣጫ ተግባራዊ ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጥላዬ ዘውዴ፤ ዲጂታል ክህሎትን በአዎንታዊ መንገድ በማጎልበት የልማት ማሳለጫ አቅም ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ የትምህርት ሥርዓትን ማጠናከር የተማሪዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማጎልበት የላቀ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የኮከብ ዲጂታል ፕላትፎርምንም የትምህርት ባለድርሻ አካላት የሕጻናትን የዲጂታል ክህሎት ማበልጸግ በሚያስችል መልኩ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የኮከብ ዲጂታል ፕላትፎርም መስራች ማህሌት ስዩም በበኩላቸው፤ መተግበሪያው ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን የንባብ ባህል ለማዳበር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህም መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት መነሻ በማድረግ የታዳጊዎችን የፈጠራ ተነሳሽነት የሚያሳድግ ወሳኝ የፈጠራ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።