ቀጥታ፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በቴክኖሎጂ የማጠናከር ተግባራት እየተከናወነ ነው

ጅግጅጋ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በቴክኖሎጂና ሌሎች መስኮች የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሠ መሥተዳድር ኢብራሂም ዑስማን ገለጹ።


 

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት “ወደ ቀበሌ መድረስ” በሚል መሪ ሐሳብ 2ኛው ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ሪፎርም ንቅናቄ መድረክ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ መካሄድ ጀምሯል።

በዚሁ ወቅት ምክትል ርዕሠ መሥተዳድሩ እንዳሉት፤ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች መስኮች ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።



 
ማኅበራቱ በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በክልሉ መታረስ የሚችል 10 ሚሊየን ሔክታር መሬት እንዳለ ገልጸው፤ በእንስሳት ሀብት፣ በሌማት ትሩፋትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ምርታማ ለመሆን የሚያስችሉ ዕድሎች መኖራቸውን አመላክተዋል።


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት በሁሉም መስኮች የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
 
የሀገር ኢኮኖሚን መገንባት የሚቻለው በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍና በዜጎች ድምር ዐቅም መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል።


 

የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሪፎርም ንቅናቄን በቀበሌ ደረጃ ለማድረስ እና ከገጠር ልማት እና ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ጋር ለማቀናጀት ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።



 
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ሙመድ በበኩላቸው፤ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተጨባጭ ሃብት በማፍራት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተጨማሪ ዐቅም እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሪፎርምን በቀበሌ እና በማኅበረሰብ ደረጃ ወደ መሬት ለማውረድ እና በገጠር ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ውጤት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም