ቀጥታ፡

በኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ውስጥ የሴቶች ንቁ ተሳትፎ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ግንባታ የጎላ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፡- ሴቶች በተለያየ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሰማራት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ግንባታ ሚናቸው የጎላ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስገነዘበ።

‎ዓለም አቀፉ የኢንዱስትሪ ሴቶች ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ “ሴቶች የወደፊት ኢንዱስትሪን በመቅረጽ ላይ” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

‎‎የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ሴቶች በተለያየ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሰማራት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ግንባታ የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል።

‎ሴቶችን ከማብቃት ጎን ለጎን በሙሉ ዐቅማቸውና በእኩልነት በዘርፉ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ፤ በአምራችነት፣ በአመራርነትም ሆነ በፈጠራ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ሁላችንም በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

‎የበዓሉ መከበር በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች የበለጠ ትኩረት እንዲያገኙ፣ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንዲፈቱ እና በዘርፉ ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ አስተዋፅዖ እንዳለው ጠቁመዋል።

‎በተጨማሪም ለሥርዓተ ጾታ አካታችነትና ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት ያለንን ቁርጠኛነት የሚያጠናክር ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት /UNIDO/ በዓሉ በኢትዮጵያ እንዲከበር ላበረከተው ሚና አመሥግነዋል።

‎የዩኒዶ ተወካይና የሰብ ሪጅናል ጀነራል ዳይሬክተር ስቴፈን ካርግቦ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋማቸው ሴቶችን አካታች ያደረገና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት እውን ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠራ ገልጸው፤ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም