ሁለተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የ2018 ዓ.ም ሁለተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ በራስ ኃይሉ የትምህርት እና ስፖርት ስልጠና ማዕከል ዛሬ መካሄድ ተጀምሯል።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከ12 ክለቦች የተወጣጡ 120 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ።
አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ኦሜድላ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ዩናይትድ ስዊት፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ ወወክማ፣ ኤቲ፣ ተወልደ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀድያ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው።
በወንዶች ከ48 እስከ 86 ኪሎ ግራም፤ በሴቶች ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ውድድሩ የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የውድድሩ አላማ በሁለቱም ጾታዎች ለኢትዮጵያ ቦክስ ብሔራዊ ቡድን የሚሆኑ ተወዳዳሪዎችን መምረጥ ነው።
ውድድሩ በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ በመሆኑ ለቦክስ ክለቦች የውድድር አማራጭን እንደሚያሰፋ ተናግረዋል።
የዘንድሮው የመጀመሪያ ውድድር በህዳር ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም መካሄዱን አስታውሰዋል።
ሶስተኛው ውድድር በግንቦት ወር 2018 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ፣ አራተኛው በሰኔ ወር አጋማሽ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም ነው የጽህፈት ኃላፊው የጠቆሙት።
በከተሞቹ የሚካሄዱት ውድድሮች አጠቃላይ ውጤት ተደምሮ በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ክለቦች እንደሚለዩም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድር እና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ ኢንስትራክተር ካሳሁን ምንተስኖት በበኩላቸው፤ ውድድሩ ለታዳጊ ስፖርተኞች የውድድር ተሳትፎ በር የሚከፍት እና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
በውድድሮቹ ላይ የሚገኙ ተወዳዳሪዎች ኢትዮጵያን በመወከል የሀገርን ስም የማስጠራት እድል እንደሚያገኙም ተናግረዋል።
በቀጣይ በግል ተቋማት መካከል የሚደረግ የቦክስ ውድድር ለማዘጋጀት መታቀዱንና ይህም የውድድር አማራጮችን ለማስፋት እንደሚያስችል ነው ያብራሩት።
የቦክስ ፌዴሬሽን ከክልሎች እና ከክለቦች ጋር በመተባበር በታዳጊዎች ስፖርት ልማት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው የቁሳቁስ ድጋፍ እና ስልጠናን ጨምሮ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እያሱ ወሰን አማካኝነት የአህጉሪቷን የቦክስ ልማት ለማሳደግ እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በፕሬዝዳንትነቷ የቦክስ ስፖርት ስራዋን ለአፍሪካ እና ለተቀረው ዓለም የማሳየት እድል ማግኘቷንም ነው ያነሱት።
በዛሬው የውድድር መክፈቻ 21 የማጣሪያ ውድድሮች ተካሂደዋል።
የ2018 ዓ.ም ሁለተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
አዲስ አበባ ፖሊስ በ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በሁለቱም ጾታዎች በካታጎሪ ኤ የውድድር አይነት አጠቃላይ አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች በካታጎሪ ቢ አጠቃላይ ማሸነፉ አይዘነጋም።