ቀጥታ፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቶታል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ  ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፍጹም ጥላሁን በ71ኛው ደቂቃ ግቧን ከመረብ ላይ አሳርፏል። 


 

በሊጉ ዘጠነኛ ድሉን ያስመዘገበው  ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ35 ነጥብ ደረጃውን ከ14ኛ ወደ 10ኛ ከፍ አድርጓል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ ከነበረበት 13ኛ ደረጃ ወደ 14ኛ ዝቅ ብሏል።

አዳማ ከተማ ባለፉት ስምንት የሊጉ ጨዋታዎች ከድል በመራቅ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ይገኛል።  

ጨዋታውን ተከትሎ የ28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ተጠናቋል። 

ፕሪሚየር ሊጉ በኢትዮጵያ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ምክንያት የሚቋረጥ ሲሆን፤ በ29ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሚያዝያ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ውድድር ይመለሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም