ቀጥታ፡

በመቱ ካርል ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው

መቱ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ):- በመቱ ካርል ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው።

ሆስፒታሉ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ከሁለት ሺህ የሚልቁ ታካሚዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

በህክምና ማስጀመሪያው ላይ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የዓይን ሕክምና ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሙሳ ሱልጢ እንደገለፁት፤ ቢሮው ለዓይነ-ስውርነት ምክንያት የሆነውን የዓይን ሞራ ግርዶሽ ለመከላከል ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከዓይን ሞራ ግርዶሽ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የዓይን ጤና ችግር ለመከላከል በተደረገው ጥረት ከ36 ሺህ በላይ ታካሚዎች የነፃ ቀዶ ህክምና አገልግሎት በማግኘት ብርሃናቸው መመለሱን አውስተዋል።

አሁን ላይም ቢሮው 'ፍሬድ ሆሎውስ ፋውንዴሽን' ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር በመቱ ካርል ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የዓይን ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና እየሰጠ ነው ብለዋል።

የአሁኑ ዘመቻም በመቱ ከተማና በኢሉአባቦር ዞን ሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ሕክምናው የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን ጨምሮ የአጎራባች አካባቢዎች ታካሚዎችን ተደራሽ እንደሚያደርግም አክለዋል።

በኢሉአባቦር ዞን ህብረተሰቡን በማስተማርና በመቀስቀስ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አገልግሎትን እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምትኩ ድንቅነህ ናቸው። 

በዚህም በሆስፒታሉ እየተሰጠ በሚገኘው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት የተደረገላቸው ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ የዞኑና የመቱ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

የዓይን ሞራ ግርዶሽ ችግር ያለባቸው ታካሚዎች ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ መታከም እንደሚችሉ ጠቁመው ችግሩ ያልተከሰተባቸው ደግሞ የግልና የአካባቢ ንፅህናን በመጠበቅ ችግሩን ሊከላከሉ ይገባል ብለዋል። 

በሕክምናው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ ዓለሙ ጂራታና ወይዘሮ አይናለም ብርሃኑ ለመታከም አቅም ስላልነበራቸው ከችግሩ ጋር ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን ተናግረው ህክምናውን በነፃ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሽብሩ ከበደ በበኩላቸው ህክምናውን ለማግኘት መምጣታቸውን ጠቁመው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምናው የዓይን ብርሃናቸውን እንደሚመልስ ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ነፃ የሕክምና እድል በማመቻቸቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም