የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት የአጋር ድርጅቶች አስተዋጾ የሚበረታታ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት የአጋር ድርጅቶች አስተዋጾ የሚበረታታ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አርባ ምንጭ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት የአጋር ድርጅቶች አስተዋጾ የሚበረታታ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጋር በመሆን በአርባ ምንጭ ከተማ ያስገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ተዘጋጅቷል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በሜሪ ጆይ ራዕይ የተጀመረው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ከፍተኛ አስተዋጾ እያበረከተ ይገኛል።
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነ ባለው ተግባር የበርካታ ወገኖችን ህይወት እየታደገ እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን እያገዘ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል።
ማዕከሉ አገልግሎቱን ለማሳለጥ ለሚያደርገው ጥረት የክልሉ መንግስት በቅርበት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ማዕከል ማህበረሰቡ በቅርበት ሕክምና እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ ሲታከም ሊያወጣ የሚችለውን ወጪ ያስቀራል።
ማዕከሉ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የኩላሊት እጥበት ማሽኖች፣ የመድሃኒት ቤት፣ መኝታ አልጋዎችና የህክምና አገልግሎት መስጫ ክፍሎች አሟልቶ የተገነባ መሆኑንም አስረድተዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር)፤ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የተሰማራበት ሰው ተኮር ልማት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ መገንባት ጤናማና አምራች ዜጋን ከመፍጠር ባለፈ መንግስት እያካሄደ ላለው የጤና ልማት ስኬት ጉልህ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
ለኩላሊት እጥበት ማዕከሉ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ተመላክቷል፡፡