ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከባንግላዲሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሃሊሉር ራህማን ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከባንግላዲሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሃሊሉር ራህማን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከባንግላዲሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሃሊሉር ራህማን ጋር ተወያይተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ ኤዥያና ፓስፊክ አገሮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያና ባንግላዲሽ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።
ለአብነትም በንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን እያጠናከሩ መሆኑን በማንሳት፤ የባንግላዲሽ ባለሃብቶች በጨርቃ ጨርቅ፣ መድኃኒት ኢንዱስትሪና መሠል ዕድሎች ኢንቨስት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከባንግላዲሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሃሊሉር ራህማን ጋር ያደረጉት ውይይትም የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
በውይይቱም ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ኢትዮጵያ እና ባንግላዲሽ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል ብለዋል።
በቀጣይም የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት የበለጠ በማጠናከር የሕዝብ ለሕዝብ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ማስገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።
የባንግላዲሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሃሊሉር ራህማን፥ የሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር በከፍተኛ ሁኔታ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል ብለዋል።
ሀገራቸውም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን እንዳነሱ ተናግረዋል።
በቀጣይም የኢትዮ-ባንግላዲሽን የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር አበክረው እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል።