የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018(ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከአውሮፓ ሕብረት የዓለምአቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲከላ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም፥ በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ዘመናት የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በዚሁ ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር ነው ብለዋል።
ሕብረቱ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኃይል ልማት በመደገፍ እያበረከተ ለሚገኘው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም የአውሮፓ ሕብረት ኢንቨስትመንቶች የኢትዮጵያን የልማት ዕድሎች በመጠቀም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና የጋራ ተጠቃሚነት ገንቢ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ሕብረት መካከል አስተማማኝና ተዓማኒነት ያለው ወዳጅነት የጋራ ዕድገትን በሚያስቀጥል መልኩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ተገማችና ዕምነት የሚጣልበት ወዳጅነቶችን ለማጎልበት በቁርጠኝነት የምትሰራ ሀገር መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲከላ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገት እየገነቡ ከሚገኙ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካና ለአጠቃላይ አህጉሪቱ መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ሀገር መሆኗን በመጥቀስ ሕብረቱ የኢትዮጵያን የብልፅግና ግስጋሴ በመደገፍ የልማት አጋርነቱን እያስቀጠለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በገጠር የኃይል ልማት ተደራሽነት ላይም የአውሮፓ ሕብረት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ሕብረቱ ለኢትዮጵያ ልማት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ለማቅረብ መወሰኑን አረጋግጠው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕብረት መፂኢ ዕድል ለአውሮፓ አስፈላጊ በመሆኑ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
በቀጣይም ታሪካዊና ጠንካራ ወዳጅነትን በማስቀጠል የጋራ ጥቅምና ዘላቂ ወዳጅነት ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።