ቀጥታ፡

የሚበጀንን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ወስደናል - የሰመራ ሎጊያ ከተማ ሴቶች

ሰመራ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይበጀናል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን የሰመራ ሎጊያ ከተማ ሴቶች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ዘሃራ ያሲን ፤ ይበጀኛል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።


 

ወይዘሮ ከይሪያ መሐመድ በበኩላቸው፣ የሴቶች በምርጫ መሳተፍ ያላቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ከማሳደጉም በላይ ለሴቶች ተጠቃሚነት መረጋገጥ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።


 

ይህንንም በመረዳት በምርጫ ቦርድ በተራዘመው ተጨማሪ ቀናት ተጠቅመው የሚበጃቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

አሚናት ሰይድ እና አሚናት አደም የተባሉ አስተያየት ሰጪዎችም እንዲሁ በዘንድሮው ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ ወስደዋል። 


 

በካርዳቸውም የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት ሊሠራ የሚችል ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች በቀሪ ቀናት የምርጫ ካርድ በመውሰድ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ቦርዱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም