ቀጥታ፡

የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ወልቂጤ ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ባለፉት የለውጥ አመታት ያሉትን ፀጋዎች በመጠቀም የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የተገኙ ትሩፋቶችን የሚደግፍ ህዝባዊ  ሰልፍ ዛሬ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።


 

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ፤ በለውጡ ዓመታት በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም በግብርና፣ በአረንጓዴ ልማት እንዲሁም  በጤና፣ በአገልግሎት ተደራሽነትና በተለያዩ ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት በማከናወን ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መደረጉ የለውጡ መንግስት ትሩፋት መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ከተደራጀ በአጭር ጊዜ ውስጥ ህዝብን በማሳተፍ በተሰራው ተግባር የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

የተገኙ የለውጥ ትሩፋቶችና ውጤቶችን በህዝብ ተሳትፎ  አጠናክሮ የማስቀጠል ተግባር በትኩረት እንደሚከናወንም አስታውቀዋል ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ የለውጡ አመታት የልማትና እድገት አቅጣጫ ትክክለኛ መሰረት የያዘበትና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን አንስተዋል፡፡


 

በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚው መስክ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል ።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተሳተፉ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዳንኤል ዲባባ ሀገራዊ ለውጡን በመደገፍና የተመዘገቡ ትሩፋቶቹን ለማስቀጠል በድጋፍ ሰልፉ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በለውጡ አመታት የሀገር ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ መሰረት የተጣለበት ፣በየደረጃው የህዝብ ተጠቃሚነት ያደገበት ነው ያሉት ደግሞ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ነዒማ አክመል ናቸው ።

በለውጡ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም