መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያለ እንግልት የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለማግኘት አስችሎናል - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያለ እንግልት የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለማግኘት አስችሎናል
ሚዛን አማን፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያለ እንግልት የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለማግኘት አስችሎናል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በማዕከሉ የንግድ ፈቃዳቸውን ለማሳደስ የተገኙት አቶ መሐመድ ሁሴን፤ ያለ እንግልት የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለማግኘት መቻላቸውን ነው የሚገልጹት።
አገልግሎቱ ከወረቀት ንኪኪ የጸዳ ከመሆኑም ባሻገር ቀልጣፋና የደንበኞችን ክብር በጠበቀ መንገድ የሚከናወን መሆኑም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ይህም መንግሥት መልካም አስተዳደር ለማስፈን እና የሕዝብ እንግልትን ለመቀነስ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
ወይዘሮ እርጎዬ ሽፈራሁ የተባሉ ተገልጋይ በበኩላቸው በማዕከሉ እንግልት ሳይኖር በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ነው የሚገልጹት።
በመሶብ የአንድ ማዕከል በአንድ ቦታ ጊዜና ገንዘብን ቆጥቦ ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት በመቻላቸው ከእንግልት መዳናቸውን ነው ያመለከቱት።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በማውጣት ላይ የነበረው ወጣት ኤልያስ አዘነ በበኩሉ፤በወራት ቀጠሮ የማያልቁ ጉዳዮችን በደቂቃዎች መጨረስ እየተቻለ በመሆኑ ቴክኖሎጂውን በተሻለ መንገድ በማልማት አገልግሎቱን አስተማማኝ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን አመላክቷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የቴክኖሎጂ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አሕመድ ሁሴን፤ በማዕከሉ በአምስት ወራት ብቻ ከ22 ሺ ለሚበልጡ ዜጎች አገልግሎት መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡
ከተገልጋዮች በሲስተም የተወሰደ የጥናት መረጃ እንደሚያመለክተውም የደንበኞች እርካታ መጠንን 97 ነጥብ 8 በመቶ ለማድረስ መቻሉን ገልፀዋል።
በክልሉ ለዜጎች ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ጠንካራ የዲጂታላይዜሽን ሲስተም የመገንባቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የሚዛን አማን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋም ውስጥ 9 የክልልና የፌዴራል ተቋማት 38 አገልግሎቶቻቸውን እንዲሰጡ ተደርጎ የተደራጀ ነው።