ለመራጭነት የሚያበቃንን ካርድ በመውሰድ ሕገ-መንግስታዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
ለመራጭነት የሚያበቃንን ካርድ በመውሰድ ሕገ-መንግስታዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመውሰድ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፣ የዘንድሮው የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመከናወን ላይ ይገኛል።
ቦርዱ መጀመሪያ ላይ ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ በማሻሻል፣ ህዝቡ በስፋት እንዲመዘገብ ዕድል ለመስጠት ሲል የበዓል ቀናትን ሳይጨምር ምዝገባው እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲራዘም ማድረጉ ይታወቃል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን በተግባር ለመጠቀም የምርጫ ካርዳቸውን ወስደው ለድምፅ አሰጣጡ ቀን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
በምርጫ ጣቢያዎች ያለው የምዝገባ ሂደቱ ምቹና ቀልጣፋ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ ጌራ ወርቁ እንዳሉት፤ ካርዴን ወስጃለሁ፤ ለሀገር ግንባታና ለለውጥ ይጠቅማል የምለውን ለመምረጥ ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
ምዝገባውን በአቅራቢያቸው ያለ ምንም እንግልትና የጊዜ መባከን ማከናወናቸውን ጠቁመው፣ ሌሎች ዜጎችም በቀሪው ጊዜ ተመዝግበው መብታቸውን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ወርቁ ወልደሌዛ በበኩላቸው ሀገርን ያሳድጋል፣ ልማትን ያፋጥናል፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብለው ለሚያምኑበት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
አቶ ለማ በዳዳም በተመሳሳይ ምርጫ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ ሂደቱ ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ ቁልፍ ሚና ስላለው ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ምርጫ የመጪውን ትውልድ የወደፊት ተስፋ ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፣ ለዚሁ ተግባር ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አበበች ከበደ ናቸው፡፡
7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይታወቃል።