የኢትዮጵያ ግዙፍ የግብርና ኢንቨስትመንት አቅም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ግዙፍ የግብርና ኢንቨስትመንት አቅም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ያላት ሰፊ የግብርና ሃብት አቅም በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተወዳዳሪነት እያሳደገው መሆኑን በኢትዮጵያ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩት የሕንድ ባለሃብት ጋጀንድራ ሲንገህ ማንፑራ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ተግባራዊ ያደረገቻቸው የሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እያመጡ ነው።
በተለይም በምግብ ራስን ለመቻልና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ተቀይሰው ሥራ ላይ የዋሉ እንደ የስንዴ ልማት ዓይነት ኢኒሼቲቮች ተጠቃሽ ናቸው።
የስንዴ ምርት የሀገር ውስጥ ፍጆታን በመሸፈን ወደ ውጭ መላክ መጀመሩ ኢኒሼቲቩ ፍሬያማ መሆኑን አመላካች ነው።
በግብርና ኢንቨስትመንት በኩልም ባለኃብቶችን የሚያበረታቱ ምቹ ሁኔታዎች ከመፍጠር ባለፈ በዘርፉ ያላት እምቅ አቅም የሀገር ውስጥና የውጭ ባለኃብቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እየሳበ ነው።
የሕንድ ባለሀብት ጋጀንድራ ሲንገህ ማንፑራ፤ በደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ኬኒያ፣ ዛምቢያና በሌሎች ሀገራት የኢንቨስትመንት ዳሰሳ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝትም ሀገሪቷን ለግብርና ኢንቨስትመንት ተመራጭ በማድረግ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም የአቮካዶ ምርትን በማሳደግ ለተለያዩ የዓለም ገበያዎች ለማቅረብ በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም በሙዝ፣ በእንጆሪ፣ በቅመማ ቅመም እና በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ኢንቨስትመንታቸውን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
አሁን ላይ በ500 ሺህ ዶላር መነሻ ካፒታል እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ባለሀብቱ፤ በቀጣይም ኢንቨስትመንታቸውን በሦስት እጥፍ የማሳደግ ዕቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የግብርና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ የድጋፍና የክትትል ሥርዓት እንዲሁም አስቻይ ምኅዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።
መንግሥት ከመሬት አቅርቦት በተጨማሪ እንደ መንገድ፣ ኤሌክትሪክና የውሃ አቅርቦት ያሉ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት የአልሚዎችን አቅም እያጠናከረ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ምቹ ሁኔታ፣ ሀገሪቷን የዓለም አቀፍ ገበያ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል አቅም እንዳላት ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።