ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የወሰደቻቸው ተጨባጭ እርምጃዎች ውጤት እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የወሰደቻቸው ተጨባጭ እርምጃዎች ውጤት እያስገኙ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የወሰደቻቸው ተጨባጭ እርምጃዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ከአፍሪካ የሚቲዎሮሎጂ ሶሳይቲ ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀውን ሳይንሳዊ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዚዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለዘርፉ ተስማሚ የሆኑ የኃይል አማራጮችንና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በተግባር እያከናወነች ትገኛለች፡፡
ለዚህም እንደ አብነት ከሚጠቀሱት መካከልም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የታዳሽ ኃይል ልማት ተምሳሌትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የደን ልማት ስራዎች ተጨባጭ መፍትሄዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ተጽዕኖውን ለመቋቋም የጋራ ጥረትና ትብብር መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከኮንፈረንሱ ለአፍሪካ ውጤታማ የሆኑ ሳይንሳዊ መፍትሄዎች እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ የሚቲዎሮሎጂ ሶሳይቲ የቦርድ ሰብሳቢ ቡሩሃኒ ናይንዚ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሶሳይቲው የተቋቋመው ሀገር አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ማህበራትን ለማጠናከርና በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ለማስተሳሰር መሆኑን ገልጸዋል።
ሳይንሳዊ ኮንፈረንሱ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአየር ትንበያና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ተቋማትና ባለድርሻ አካላትን እንደሚያገናኝም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የልምድና የዕውቀት ልውውጥ በማድረግ የባለሙያዎችን አቅም እንደሚገነባ ጠቅሰው በአፍሪካ የሚቲዎሮሎጂ ሳይንስ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
ይህ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ያላትን ተሞክሮ ለማካፈል እንደሚረዳም ተጠቁሟል፡፡