ቀጥታ፡

ምርጫ ቦርድ ባመቻቸው ተጨማሪ ቀናት የመራጭነት ካርድ ወስደን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል-ሴቶች

አርባምንጭ ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የምርጫ ቦርድ ባመቻቸው ተጨማሪ ቀናት የመራጭነት ካርድ ወስደው የመምረጥ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶች ገለጹ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአርባምንጭ ከተማ ሴቶች እንደገለፁት፤ የምርጫ ቦርድ ያመቻቸውን ተጨማሪ የመራጭነት ካርድ የመውሰጃ ቀናት በመጠቀም ካርድ ወስደዋል፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አክለዋል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አስናቀች አባይነህ፤ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ተጨማሪ ቀናት በመጠቀም  ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።


 

በዚህም ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን የመጠቀም ተጨማሪ እድል ማግኘታቸውን ጠቅሰው ካርድ ያልወሰዱ ሰዎችም በቀሪ ቀናት ካርድ ወስደው መብታቸውን እንዲጠቀሙ መክረዋል።

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ነፃነት ኬንቲቤ በበኩላቸው፤ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።


 

በካርዱም ለሀገር ልማትና አንድነት የሚበጅን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አመልክተው ለምርጫው ሰላማዊነትና ፍትሃዊነት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ መብቴን ለመጠቀም የመራጭነት ካርድ ወስጃለሁ ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ጽዮን ጳውሎስ የተባሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ናቸው።


 

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ነገ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙም መክረዋል።

7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም