ቀጥታ፡

በዞኑ ለመጪው መኸር ሰብል ልማት የሚውል የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ ነው

ደሴ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ለመጪው የመኸር ሰብል ልማት የሚውል ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በማስገባት ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ለ2018/19 የመኸር ሰብል ልማት ተገቢውን ግብዓት በማቅረብ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

በዚህም ለመጪው ምርት ዘመን ከ644 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ በተደረገ ጥረት እስካሁን ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል።


 

ወደ ዞኑ ከገባው ውስጥም ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ወደ ወረዳዎች በማድረስ ቅድሚያ ለሚዘሩትና ሩቅ አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው ብለዋል።

ቀደም ብሎ ማዳበሪያው መሰራጨቱ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የዘር ሥራውን በወቅቱ ከማከናወን ባለፈ ምርታማነቱን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

በአልብኮ ወረዳ የ014 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብዱ እንድሪስ በሰጡት አስተያየት፣ ለቀጣይ የመኸር እርሻ ከሚያስፈልጋቸው እስካሁን 3 ኩንታል ማዳበሪያ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።


 

በዘንድሮው የመኸር ዘመን ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በተለያየ ሰብል ለማልማት እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመው ማዳበሪያው ቀድሞ በእጃችን መግባቱ ያለስጋት የእርሻ ስራችንን ለማከናወን ያግዘናል ብለዋል። 

በደቡብ ወሎ ዞን በ2018/19 የምርት ዘመን ከ432 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም