ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የኢኮኖሚ አጋርነታቸውን ያጠናክራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የኢኮኖሚ አጋርነታቸውን ያጠናክራሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የፀደይ ስብሰባ ጎን ለጎን በዋሽንግተን ዲሲ ከፈረንሳይ ግምጃ ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የልማት ትብብር ይበልጥ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበርም ተመላክቷል።
ፈረንሳይ የመንግሥታት አበዳሪዎች ኮሚቴን በሊቀ መንበርነት በመራችበት ወቅት በኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ ሂደት ላይ ላበረከተችው አስተዋጽኦም ሚኒስትር አህመድ ሽዴ አመስግነዋል።
ሁለቱ ሀገራት በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በዕዳ መልሶ ማዋቀር ሂደት ላይ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ይህም አዳዲስ የፋይናንስ ፍሰቶችን ለማምጣትና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ኢዜአ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመላክታል።