ቀጥታ፡

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራዎች ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ የፀደይ ወቅት ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል።

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፓስካል ዶኖሆ ጋር ውይይት አድርጓል።

ሚኒስትሩ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ (Homegrown Economic Reform Agenda) የተመዘገቡ ውጤቶችን ያብራሩ ሲሆን፤ በተለይም በኢኮኖሚ መረጋጋትና በመዋቅራዊ ሽግግር ረገድ የተመዘገቡ ስኬቶችን አንስተዋል።

 

ኢትዮጵያ ወደ ግል ዘርፍ መር የኢኮኖሚ እድገት በምታደርገው ሽግግር፣ የግል ካፒታልን ማሰባሰብ አሁን ላይ ዋነኛው ትኩረት መሆኑን ሚኒስትሩ አፅንኦት የሰጡት ጉዳይ ነው።


በተጨማሪም ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት (COP32) ጉባኤን ለማስተናገድ እያደረገችው ስላለው ዝግጅት ለዳይሬክተሩ ገለጻ አድርገዋል።

ጉባኤው የኢትዮጵያን የአየር ንብረት መቋቋም አቅምና የአረንጓዴ ልማት ቃል ኪዳኖችን እውን ለማድረግ ያለውን ጉልህ ፋይዳ ጠቁመዋል።

የዓለሞ ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፓስካል ዶኖሆ በበኩላቸው የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያደርጋቸውን ድጋፎች ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኑንም አመልክተዋል።

ዳይሬክተሩ ለኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤ ዝግጅትም ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

Boost this post to get more reach for Ethiopian News

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም