ቀጥታ፡

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው

ቦንጋ ፤ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህብረተሰቡንና የልማት አጋሮችን በማሳተፍ የተከናወኑት ተግባራት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ የመንግስትና የፓርቲ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል ።


 

የክልሉ  ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር  ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህብረተሰቡንና የልማት አጋሮችን በማሳተፍ የተከናወኑት ተግባራት ለህዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ናቸው። 

በመሰረተ ልማት፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በግብርና፣ በስራ እድል ፈጠራ ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች  በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የተመዘገቡ ልማቶች  አበረታች  ቢሆኑም  ከክልሉ የመልማት አቅም አንፃር ገና ሰፊ ስራ የሚጠይቅ በመሆኑ  ይበልጥ መትጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህም የክልሉን  አመራሮችና ሰራተኞች  እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በማቀናጀት  ተከታታይነት ያለው ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባም አክለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመንግስትም ሆነ በፓርቲ የተመዘገቡ ውጤቶችን  ማስቀጠል ይገባል ያሉት ደግሞ  የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው።


 

በተለይም አመራሩ ስራን  በመገምገምና  በቅንጅት በመስራት እንዲሁም ህብረተሰቡን በማስተባበር የመጡ ውጤቶችን ማስቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም