ኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከኦስትሪያ የአውሮፓ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሚኒስትር ቢት ሜይንል ራይዚንጀር ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው የሁለትዮሽን ግንኙነት የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ ባህል እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት መመሥረት የሚያስችል ገና ያልተነካ የትብብር አቅም እንዳለ አንስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ለሚኒስትሯ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
በታዳሽ ኃይል፣ በማምረቻው ዘርፍ፣ በቱሪዝም እና በዲጂታል መሠረተ ልማት ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎች መኖሩን አብራርተዋል።
ሚኒስትር ቢት ሜይንል ራይዚንጀር በበኩላቸው ኦስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር መስኮች የማስፋት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
በአውሮፓ-ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረም ላይም የአገራቸው ኩባንያዎች በስፋት መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
ሁለቱ አገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በሌሎች ዓለም ዓቀፍ የትብብር መድረኮች በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በፍልሰት እና በዘላቂ የልማት ግቦች ዙሪያ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ ለ120 ዓመታት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው።