ኢትዮጵያ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያጠናክሩ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው ሲሉ የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆዜፍ ሲከላ ገለጹ።
የአውሮፓ ሕብረት እና ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረም "ዓለም አቀፍ የገበያ መግቢያ አቅምን መጠቀም" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆዜፍ ሲከላ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መስራች፣ የቡና መገኛ፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነች ታሪካዊ ሀገር ናት።
ኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያጠናክሩ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ መዳረሻዋ የት እንደሆነ በግልጽ አሳይታለች ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰረት ልማትና የዲጂታል መሰረተ ልማት ይፈልጋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ሕብረቱ በገጠር መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት እና ኢትዮጵያ ቢዝነስ ፎረም በንግድ ድርጅቶች መካከል፣ በመንግሥት እና በንግድ ድርጅቶች መካከል ገንቢ ውይይት ማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ዛሬ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ከበጀት ድጋፍ ስምምነቱ ባሻገር የ150 ሚሊዮን ዩሮ የዲጂታል ኢኮኖሚ ስምምነት መፈረሙን ገልጸዋል፡፡
ይህም በዲጂታል መሰረተ ልማት፣ ክህሎትና አስተዳደር በጋራ ማዕቀፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አብራርተዋል።
የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሀፊ ዋምኬሌ ሜኔ፤ አፍሪካ ከአራት ሺህ በላይ የአውሮፓ ኩባንያዎች በመሳተፍ በዓለም ቀዳሚዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ ትብብር በአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ የተበጣጠሰ የእሴት ሰንሰለት ባለው የዓለም ገበያ በአፍሪካ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ የቢዝነስ ስራዎችን የሚያቀላጥፉ የጉምሩክና የፋይናንስ ስርዓቷን እያዘመነች መሆኑን ጠቅሰው፤ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት መፈጠሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ትርጉም ያለው ሪፎርም በማድረግ ሀገሪቷን በአፍሪካ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት አድርጓታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ቁልፍ የፋይናንስ ተቋማትን አቅም በማጠናከር የተሳለጠ የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡