ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዘመናዊ አሰራሮችን በመተግበር በሀገር ግንባታ ሂደት የበኩሉን እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዘመናዊ  አሰራሮችን በመተግበር በሀገር ግንባታ ሂደት የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) አመለከቱ፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የ75ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ በዓል መክፈቻ ሥነ ሥርዓት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል።      


 

አስተዳደሩ ከምስረታው ጀምሮ አሁን የደረሰበትን ልህቀት ስኬቶችና ተሞክሮዎችን የሚያስቃኝ አውደ ርዕይም በማዕከሉ ተከፍቷል።              

የተለያዩ ከያኒያንም በዓሉን በማስመልከት ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን አቅርበዋል።    

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አስተዳደሩ በሀገር ግንባታ ሂደት በአርዓያነት የሚጠቀስ አስተዋጽኦ አበርክቷል።      

በተቋም ግንባታ በኩልም አስተዳደሩ ምሳሌ የሚሆን ተግባራትን አከናውኗል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለዘርፉ ዕድገት ጠንካራ የግል ተቋራጭና አማካሪዎች እንዲፈጠሩ የማይተካ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።   


 

የዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ባለሙያዎችም እንዲበቁ በማድረግ ረገድ ተቋሙ ያከናወናቸው ተግባራትም በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገር የመገንባት ሂደቱን ውጤታማ በሆነ መሰረት ላይ እንዲቀመጥ አስችሏል ብለዋል።     

አስተዳደሩ በቀጣይም ዘመኑን የዋጁ አሰራሮች በመከተልና ጥናትና ምርምሮችን መሰረት በማድረግ ለላቀ ውጤት ሊተጋ እንደሚገባም አመልክተዋል።  

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን በበኩላቸው፤ አስተዳደሩ ዘመኑን የዋጁ አሰራሮችን በመከተል ብልፅግናን የሚያረጋግጡ ወጤታማ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።  


 

ለውጤት የበቁ ዘመናዊ የፍጥነት መንገዶች፣ የተለያዩ ድልድዮች እንዲሁም ተቋሙ የተከተላቸው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀሞች ለስኬቱ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።  

የአልማዝ እዮቤልዩ በዓሉ የተሻለች እና ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ቃላችንን የምናድስበት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የምህንድስናን ጥበብ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል። 

አስተዳደሩ ጥናትና ምርምርን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችንም በሰፊው ገቢራዊ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም