ቀጥታ፡

ሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ይሰራል - አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ) ፦ በሀረር ከተማ የተጀመረውን ሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭ በጥራትና ፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩና ካቢኔያቸው በክልሉ እየተገነባ የሚገኘው የሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

በዚህ ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በአው ሀኪም ተራራ ላይ እየተሰራ የሚገኘው ኢኒሼቲቩ የአዲሲቷ ሀረር አለም አቀፍ ምልክት ከመሆን ባሻገር ለክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ለቱሪዝም መዳረሻነትና ለህዝብ መዝናኛነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የፕሮጀክቱ እውን መሆን የጎብኚዎች ቆይታን በመጨመር ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አንፃርም ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በፕሮጀክቱም 1ሺህ 870 ደረጃዎች እና 2 ኪሎሜትር የሚጠጋ የመሰረተ ልማት ስራ እንደሚከናወን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ፕሮጀክቱ አካባቢያዊ ሀብቶችን በመጠቀም ይሰራል ብለዋል።

ተራራው ራሱን የቻለ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው በማድረግ ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግለት አመላክተው ለዚህም ህገ-ወጥ ግንባታን በመከላከል ረገድ በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ጠቁመው ለዚህም የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም