በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢኮኖሚ ዘርፍ በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢኮኖሚ ዘርፍ በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል
ቦንጋ፤ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢኮኖሚ ዘርፍ በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስትና የፓርቲ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የክልሉን መንግስት የስራ እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ሀላፊ ወሰነች ቶማስ እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡
በተለይም የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት በ2017/18 ምርት ዘመን በመኽር ወቅት 23 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት መሰብሰቡን አንስተው በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ደግሞ እስካሁን 154 ሺህ 279 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተከናወነው ተግባር በግብርና፣ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 93 አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ፈቃድ መሰጠቱንም አመልክተዋል።
በተለያዩ ዘርፎች ለ57 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንና ከተቋማት ጋር በመተባበር ከ658 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መመቻቸቱን አንስተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ኢኮኖሚያዊ ተግባራት የመንግስትንና የህዝብን ቅንጅት ያሳዩ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊና የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አክሊሉ ወልደሚካኤል ናቸው።
ተግባሩን ለማላቅም በቀሪ ጊዜያት የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው፤ ከመሠረተ ልማት አንፃር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች መልካም መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡትን ለይቶ ትኩረት በመስጠት የተጀመሩ ስራዎች እንዲጠናከሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።