በጠቅላላ ምርጫው ድምፅ መስጠት የሚያስችለንን ካርድ በመውሰድ ንቁ ተሳትፎ እያደረግን ነው - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላላ ምርጫው ድምፅ መስጠት የሚያስችለንን ካርድ በመውሰድ ንቁ ተሳትፎ እያደረግን ነው - ወጣቶች
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ በመውሰድ በሂደቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚያካሂደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ዜጎች ድምፅ መስጫ ካርድ እንዲወስዱ ማራዘሙ ይታወቃል።
ሁለት ቀናት በቀሩት የመራጮች ምዝገባም እስከ ሚያዚያ 09 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 46 ሚሊዮን 732 ሺህ 895 መራጮች በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ተመዝግበዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ አዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት፤ ምርጫ ሕገ መንግስታዊ የመምረጥ መብታችንን ተግባራዊ የምናደርግበት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ ነው ብለዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሕዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ወጣት አቢሲኒያ ተሻለ፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ድምፅ መስጠት የሚያስችለውን የምርጫ ካርድ መውሰዱን ተናግሯል።
ወጣት ይበልጣል ባህሩም በተመሳሳይ ሀገራዊ ምርጫ የዴሞክራሲያዊነት መገለጫ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ድምፅ መስጠት የምችልበትን የምርጫ ካርድ ወስጃለሁ ብሏል።
ፋኖስ ታረቀኝ በበኩሏ፤ ምርጫ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት የአደባባይ መድረክ መሆኑን ገልፃለች።
ካርድ ያልወሰዱ ዜጎችም ቦርዱ የሰጠውን ተጨማሪ የጊዜ ሰሌዳ በመጠቀም ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርባለች።
ጠቅላላ ምርጫው የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ ባህል የመገንባት ልምምድ ያጎለብታል ያለው ደግሞ ወጣት ደረጄ ሙሉጌታ ነው።
ለዚህም ድምፅ መስጠት የሚያስችለውን ካርድ በመውሰድ መዘጋጀቱን አረጋግጧል።
ወጣት ታደሰ አያሌው በበኩሉ፤ እንደወጣት የሃሳብ የበላይነት ባህልን በማዳበር በምርጫ ሂደት ገንቢ ሚና የመወጣት ሀገራዊ ኃላፊነት ይጠበቅብናል ሲል ነው የገለጸው።
ለዚህም በምርጫው ወቅት ድምፅ መስጠት የሚያስችለውን ካርድ በመውሰድ ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀቱን ነው የገለጸው።