በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ የአውሮፓ ሕብረትና አባል ሀገራት ኩባንያዎች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ የአውሮፓ ሕብረትና አባል ሀገራት ኩባንያዎች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ የአውሮፓ ሕብረትና አባል ሀገራት ኩባንያዎች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ገለጹ፡፡
የአውሮፓ ሕብረት እና ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረም "ዓለም አቀፍ የገበያ መግቢያ አቅምን መጠቀም" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ዘላቂ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ሪፎርም አድርጋለች።
ኢትዮጵያ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማድረግ ያላትን ዕምቅ አቅም መጠቀም የሚያስችል ለውጥ እያመጣች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ለማውጣት፣ ትብብርን ለመፍጠር፣ የገበያ አማራጮችን ለማሰስ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን መሳብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ከሪፎርሙ በኋላ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ጨምሯል፤ የዋጋ ግሽበት ቀንሷል፤ ከወጪ ንግድ የሚገኘው የምንዛሪ መጠን በእጅጉ አድጓልም ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በተያዘው ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘገብ መተንበዩን በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በመተግበር ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን እያጠናከረች መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና የዲጂታል ግብይትን ማጠናከር የሚያስችል የዲጂታል ክፍያና አገልግሎት ስርዓት ማዘመኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በብዝሀ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተመራጭ መሆኗን በመጥቀስ፣ የአውሮፓ ሕብረትና አባል ሀገራት ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በታዳሽ ሀይል፣ ቴክኖሎጂ፣ ጋርመንትና መሰል ዘርፎች መሰማራት ይችላሉ ብለዋል።
ለኢንቨስትመንት ምቹ ሥነ ምህዳርና መሰረተ ልማት በመዘርጋት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረትና አባል ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንደሚችሉ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢንቨስተሮች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።
የኦስትሪያ ሪፐብሊክ የአውሮፓና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሚኒስትር ቤአተ ማይነል ረይዚንገር ፤የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር የሚፈጠርበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዓለም ጂኦፖለቲካና ፖሊቲካዊ ሁኔታ ፈታኝ መሆኑን ገልጸው፤ ኦስትሪያ የዓለምን ንግድና ኢንቨስትመንት በር ክፍት ለማድረግ በሚደረገው ጥረት አጋር ለመሆን ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡
በኦስትሪያ የኢንዱስትሪ አቅሞችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከጣሊያን ጋር በመተባበር ለአየር ንብረት ለውጥ በማይበገር የቡና ምርት የዓለም አቀፍ መግቢያ ፕሮጀክት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ልዩ የሆነ የቡና ሥርዓት ዝግጅት እንዳላት ገልጸው፤ በኢ-ተገማች የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ከአጋራ አካላት ጋር ትብብርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተስፋ ያላት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሯ፤ የኦስትሪያና አውሮፓ ህብረት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡