ወላይታ ድቻ ድል ሲቀናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ መድን ነጥብ ተጋርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ወላይታ ድቻ ድል ሲቀናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ መድን ነጥብ ተጋርተዋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው መርሐ ግብር ወላይታ ድቻ ምድረ ገነት ሽሬን 1 ለ 0 ረትቷል።
ያሬድ ዳርዛ በ64ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በሊጉ ሰባተኛ ድሉን ያስመዘገበው ወላይታ ድቻ በ34 ነጥብ ደረጃውን ከ16ኛ ወደ 10ኛ ከፍ አድርጓል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 11ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ምድረ ገነት ሽሬ በ29 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ቡድኑ ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ከድል በመራቅ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ መድን አንድ አቻ ተለያይተዋል።
በዛብህ መለዮ በ67ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪ ሆኗል።
ይሁንና አማኑኤል ኤርቦ በ84ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፈው ጎል ለኢትዮጵያ መድን አንድ ነጥብ አስገኝታለች።
ሀሰን ሁሴን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ አብዱል ጋንዩ ከኢትዮጵያ መድን በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ42 ነጥብ ደረጃውን ከስድስተኛ ወደ አምስተኛ ከፍ አድርጓል።
ኢትዮጵያ መድን በ31 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።
በተመሳሳይ ዛሬ በተደረገ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታ ሸገር ከተማ ባህር ዳር ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።