ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ መነቃቃት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የግንባታ ግብዓትን በሀገር ውስጥ በመተካት ለኮንስትራክሽን ዘርፉ መነቃቃት ትልቅ ዕድል መፍጠሩን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ገለጹ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ሣምንት መርሃ ግብር በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል።

በዚህም "የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመሠረተ ልማት እና በኮንስትራክሽን" በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ መነቃቃት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ንቅናቄው ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ግብዓት በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎትና ዕድል ወደ ተግባር ለመለወጥ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑንም አብራርተዋል።

ይህ ንቅናቄ የሀገርን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የውጭ ምንዛሬን የሚታደጉ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት እያስቻለ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ሮቤል ፀጋዬ፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ስትራቴጂያዊ ለውጥ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ኮርፖሬሽኑ መግዛት ብቻ ሳይሆን መገንባት የሚል አዲስ መርህ በመከተል ግብዓቶችን ከመግዛት ይልቅ በሀገር ውስጥ ወደ ማምረት መሸጋገር መቻሉን ጠቅሰዋል።

በውጭ አቅራቢዎች ላይ ያለን ጥገኝነት በመቀነስ የገበያ ቁጥጥርን ማሳደግ እና የተበታተኑ የግንባታ ሂደቶችን ወደተቀናጀ  ሥርዓት ማምጣት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ የሽግግር ጉዞ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለሀገር ግንባታ ያለውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያጠናክርና ኢትዮጵያን በዘርፉ ራሷን እንድትችል የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።

የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብስራት ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የማዕድን ሀብት በመጠቀም በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታየውን የገቢ ምርት ጥገኝነት ለመቅረፍ ስልታዊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ ለሲሚንቶ፣ ለብረት፣ ለሴራሚክስ፣ ለመስታወት እና ለጌጣጌጥ ድንጋዮች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ እንደ ብረት ማዕድን፣ ማርብል፣ ግራናይት፣ ድንጋይ ኖራ፣ ጂፕሰም እና ሲሊካ-ሳንድ ያሉ እጅግ ከፍተኛና ጥቅም ላይ ያልዋሉ የማዕድን ክምችቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

እነዚህን ሀብቶች ማልማት የኢንዱስትሪ ዕድገትን ከማፋጠኑ ባለፈ፣ የውጭ ምንዛሬን ለማዳንና ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ እንደገለፁት፤ ጥራት ያላቸው የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት እንዲቻል ኢንስቲትዩቱ የበኩሉን እየተወጣ ነው። 


 

የፖሊሲ ድጋፍን ጨምሮ የጥራት መስፈርቶችን በማዘጋጀት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም