ቀጥታ፡

የኮንስትራክሽን ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ግንባታ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፡- የኮንስትራክሽን ዘርፍ እድገትን ይበልጥ በሳይንሳዊ መንገድ ለመምራት የሚያስችል የልህቀት ማዕከል ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለፁ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ  የመሠረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ሣምንት መርሃ ግብር በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል።

በዚህም "የግንባታ ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ" በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ  የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የመንገዶች፣ ድልድዮችንና የግድቦች ግንባታን በስፋት እያከናወነች ትገኛለች።

ይህም ሀገሪቱ በግንባታ ሂደት ላይ መሆኗን የሚያመላክት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እኛ ስንገነባ ሀገር ትገነባለች በሚል እሳቤ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ውስጥ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት የኢትዮጵያን ብልፅግና የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በግንባታው ሂደት የሚሳተፉ የሀገር ውስጥ የሥራ ተቋራጮችና ኩባንያዎች አቅማቸውን በማሳደግ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን አለባቸው ብለዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ዘርፉን ዘመናዊ፣ ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ፣ ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት መዘርጋት እና ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑ ተናግረዋል።

የዘርፉን ዕድገት በሳይንሳዊ መንገድ ለመምራት የልህቀት ማዕከል ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ገልፀዋል።

በግንባታው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ( ዶ/ር) በፓናል ውይይቱ ባቀረቡት ጽሁፍ ፤በኢትዮጵያ የግንባታ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን ለመቅረፍ እና ዘርፉን ለማዘመን የተቀናጀ የቁጥጥር ማዕቀፍ እና የዲጂታል አሰራር ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዘርፉ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ የቆዩና በእጅ የሚከናወኑ አሰራሮች፣ የተበታተኑ መረጃዎች እና የግልጽነት ማነስ እንደ ዋና ተግዳሮት መቀጠላቸውን አስረድተዋል።

የግንባታው ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችን፣ ደረጃዎችን እና ዲጂታል ቴክኖሎጂን ያጣመረ ሁሉን አቀፍ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቅድስት ማሞ በበኩላቸው፤ የዘርፉን አቅም ለማሳደግ የሰው ኃይል ልማት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ተቋማዊ አደረጃጀትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በአሁኑ ወቅት ወሳኝ በሆነ የለውጥ ምዕራፍ ላይ እንዳለም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም