ቀጥታ፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የልማት አጀንዳዎች ያለውን አጋርነት እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማጠናከር፣ ለሀገሪቱ የልማት የቅድሚያ ትኩረቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ ተደርጓል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ሲዲ ኡልድ ታህ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያመጡ የልማት ትብብሮችን ማሳደግን ያለመ ነው።


 

በኢትዮጵያና በአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት መረጋገጥ የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።

ባንኩ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራዎችና የረጅም ጊዜ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚጫወተው ወሳኝ ሚናም ተነስቷል።

ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የሪፎርም አጀንዳዋን ተግባራዊ በማድረግ ቀጣይነት ያለው እድገት እያስመዘገበች መሆኑን አመልክተዋል።

መንግስት ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ ለግሉ ዘርፍ መሪነት እና ለተቋማዊ ሽግግር በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ሲዲ ኡልድ ታህ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሪፎርሙ እያመጣች ያለውን ለውጥና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን የመቋቋም አቅም አድንቀዋል።


 

ባንኩ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለምትሰጣቸው የልማት ጉዳዮች የሚያደርገውን ጠንካራ ድጋፍ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ሁለቱ ወገኖች ሁሉን አቀፍ እድገትን ለማስቀጠልና የስራ እድል ፈጠራን ለማፋጠን ቁልፍ በሆኑት የኢነርጂ፣ የመሰረተ ልማት፣ የግብርና እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ዘርፎች ላይ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያና የአፍሪካ ልማት ባንክ ዘላቂ የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማምጣትና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማላቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም